ቻይና በአየር ክልሏ ላይ አሜሪካ ከፍተኛ ከፍታ ያላቸው ፊኛዎችን አብራለች ስትል ወቀሰች
ፊኛዎቹ የገቡት ለወታደራዊ ይሁን ለስለላ ዓላማ የተባለ ነገር የለም
ከቀናት በፊት አሜሪካ የቻይናን የስለላ ፊኛ ነው ያለችውን ፊኛ በጥይት መታ ጥላለች
ቻይና ሰኞ እለት እንደገለጸችው ከፈረንጆቹ 2022 ጀምሮ የአሜሪካ ከፍታ ያላቸው ፊኛዎች ያለፍቃድ በአየር ክልሏ ላይ ከ10 ጊዜ በላይ በረዋል።
ይህም የአሜሪካ ጦር ባለፈው ሳምንት የቻይና የስለላ ፊኛ ነው ያለውን ቁስ በጥይት መመታቱን ተከትሎ ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ፈጥሯል ነው የተባለው።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢን “ከባለፈው ዓመት ጀምሮ የአሜሪካ ከፍታ ያላቸው ፊኛዎች ከ10 ጊዜ በላይ በህገ-ወጥ በረራዎች ወደ ቻይና አየር ክልል ገብተዋል” ሲሉ ተናግረዋል።
ዋንግ ፊኛዎቹን ለወታደራዊ ወይም ለስለላ ዓላማ ይግቡ ያሉት ነገር የለም። ቃል አቀባዩ ተጨማሪ ዝርዝሮችንም አልሰጡም ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።
ቻይና በአየር ክልሏ ላይ ለተፈጸመባት ወረራ ምን ምላሽ እንደሰጠች የተጠየቁት ዋንግ “ኃላፊነት የተሞላበት እና ሙያዊ” ነበር በማለት መልሰዋል።
የአሜሪካ መከላከያ በቻይና ወቀሳ ዙሪያ አስተያየት እንዲሰጥ ለቀረበለት ጥያቄ ወዲያውኑ ምላሽ አልሰጠም።
የቻይና መግለጫ የመጣው አሜሪካ የቻይና የስለላ ፊኛ ነው ያለችውን ፊኛ በጥይት ከመታች በኋላ ነው።
የፊኛው ሁነት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን የቤጂንግ ጉብኝታቸውን ለሌላ ጊዜ እንዲያስተላልፉ አድርጓል።
ቻይና በበኩሏ ፊኛው መንገዱን የሳተ የምርምር ስራ ነበር በማለት ዋሽንግተን ነገሩን አጋግላለች ስትል ወቅሳለች።
ዋንግ "አሜሪካ ማድረግ የነበረባት የመጀመሪያው ነገር ፊኛውን መመልከት፣ አካሄዱን መቀየር እንጂ ግጭት መቀስቀስ አይደለም" ብለዋል።
በቅርብ ቀናት ውስጥ የአሜሪካ ጦር በሰሜን አሜሪካ ላይ ሌሎች ሶስት የበረራ ቁሶችን መቶ ጥሏል።
ቃል አቀባይ ዋንግ ስለ የቅርብ ጊዜዎቹ ሦስት በራሪ ቁሶች ምንም አይነት መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል።