አሜሪካ በ"ሰላይ ፊኛ" ምክንያት የቻይና ኩባንያዎችን በጥቁር መዝገቧ አሰፈረች
አዲሱ እገዳ ዋይት ሀውስ 'የቻይናን ትላልቅ የስለላ ስራዎች ማማጋለጥ' በሚል የገባውን ቃል የሚሳይ ነው ተብሏል
ኩባንያዎቹ ለቻይና ወታደራዊ ማሻሻያ ጥረቶች ድጋፍ አድርገዋል በሚል ነው እግድ የተጣለባቸው
አሜሪካ በ"ሰላይ ፊኛ" ምክንያት የቻይና ኩባንያዎችን በጥቁር መዝገቧ አሰፈረ
አሜሪካ ከቤጂንግ የስለላ ፊኛ መርሀ-ግብር ጋር በተያያዘ ስድስት የቻይና ኩባንያዎች የወጪ ንግድ ክልከላ በመጣል ጥቁር መዝገብ ላይ አስፍራለች።
አርብ ዕለት በአምስት ኩባንያዎች እና በአንድ የምርምር ተቋም ላይ ገደቦችን ያስታወቀው የአሜሪካ የኢንዱስትሪና የደህንነት ቢሮ፤ ተቋማቱ ኢላማ የተደረገባቸው ለቻይና ወታደራዊ ማሻሻያ ጥረቶች ድጋፍ በማድረጋቸው ነው ብሏል።
ኩባንያዎቹ በተለይም ለቻይና ህዝባዊ ጦር የኤሮስፔስ መርሀ-ግብርን ጨምሮ የበራሪ መሳሪያ እና ፊኛዎች ልማት ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተነግሯል።
ቢሮው ጦሩ እጅግ በከፍተኛ ከፍታ ላይ የሚበሩ ፊኛዎችን ለደህንነትና ለስለላ ስራዎች እየተጠቀመ ነው ሲል አክሏል።
አዲሶቹ እገዳዎች ዋይት ሀውስ የአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነትንና አጋሮችን አደጋ ላይ የሚጥሉትን የቻይና ትላልቅ የስለላ ስራዎችን ለማጋለጥና ምላሽ ለመስጠት ሰፊ ጥረቶችን እንደሚያደርግ ማሳወቁን ተከትሎ የተጣሉ ናቸው።
ባለፈው ሳምንት በአሜሪካ አየር ክልል የታየው የቻይና ፊኛ በዋሽንግተን የፖለቲካ ቁጣ መቀስቀሱን የጠቀሰው ኢንዲፔንደንት፤ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የበለጠ ስለማሻከሩ አንስቷል።
በተጨማሪም ድርጊቱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ሁለቱ ሀገራት የሻከረ ግንኙነታቸውን ፈር ለማስያዝ ወደ ቤጂንግ ሊያደርጉ የነበረውን ጉዞ እንዲሰርዙ አድርጓል ነው የተባለው።
ዋሽንግተን በዝርዝሩ ኩባንያዎችን ማካተት ለብሄራዊ ደህንነት አስጊ ናቸው የተባሉትን ለመቅጣት እና ቤጂንግ በወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዳታድግ ለማድረግ ይጠቅማል ብላለች።
ኩባንያዎች ከቻይና መንግስት ጋር በተለያዩ ዘርፎች ሠርተዋል ነዉ የተባለው።