ሩሲያና ቻይና ዶላርን በመተው የየራሳቸውን መገበያያ ለመጠቀም ተስማሙ
ቻይና ከሩሲያ ለምትገዛው ጋዝ በዩዋንና በሩብል ለመክፈል መስማማቷን ጋዝ ፕሮም አስታውቋል
ሀገራቱ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት አሜሪካና የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ላይ በጣሉት ማእቀብ ምክንያት ነው
የሩሲያ ጉዝፉ የነዳጅ ኩባንያ ጋዝፕሮም ቻይና የጋዝ ግብይትን ከዶላር ይልቅ በሩብል እና በዩዋን እንድተክፍለው የሚያስችል ስምምነት መፈራረሙን አስታወቀ።
የጋዝፕሮም ዋና ስራ አስፋጻ አሌክሲ ሚለር፤ ቻይና እና ሩሲያ የተፈራረሙት አዲሱ የክፍያ ስርዓት ሁለቱንም ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ እና አስተማማኝ ነው ሲሉ ተስምተዋል።
ከቻይና ጋር የተደረሰው አዲሱ ስምምነት ሂሳብ ለመስራት ቀላል እንደሆነ እና ለሌሎችም ምሳሌ እንደሚሆን ሚለር አክለው አስታውቀዋል።
ሁለቱም ሀገራት በዶላር መገበያየትን አቁመው መቼ በራሳቸው ገንዘብ መገበያየት ይጀምራሉ ለሚለው ግን ጋዝፕሮም ዝርዝር ከመስጠት ተቆጥቧል።
ሁለቱ ሀገራት መገበያያቸውን ከዶላር ወደ ራሳቸው የመቀየር ሂደት ሩሲያ ዶላር እና ዮሮን ጨምሮ በምእራባውያን ከሚዘወሩ መገበያያዎች ላይ ካላት ጥገኝነት የማላቀቅ አካል እንደሆነ ተነግሯል።
ሩሲያ ከዩክሬን ጋር በገባቸው ጦርነት ከምዕራባውያን 6 ሺህ ማእቀቦች የተጣሉባት ሲሆን፤ ሩሲያም ይህንን ተከትሎ ከቻይና እና ከምእራባውያን ውጪ ከሆኑ ሀገራት ጋር ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቷን ለማጠናከር እየሰራች ተገኛለች።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በያዝነው የፈረንጆቹ 2022 ላይ የአውሮፓ ደንበኞቻቸው ከሩሲያ ጋዝን መግዛት መቀጠል ከፈለጉ በጋዝፕሮም ባንክ የሩብል የባንክ ሂሳብ እንዲከፍቱ ማሳሰባቸው ይታወሳል።
ይህንን ስምምነት አልቀበል ላሉ የተወሰኑ ኩባንያዎች ሩሲያ ጋዝ ማቅረብ ያቆመች ሲሆን፤ ይህም የጋዝ እና የነዳጅን ጨምሮ የኃይል ዋጋ እንዲጨምር አድርጓል።