ሀገራቱ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት በሩሲያ ላይ በጣሉት ማእቀብ ምክንያት ነው
ሩሲያ እና ህንድ በዶላር ላለመገበያየት መስማማታቸው ተገለጸ፡፡
የሩሲያ፣ ቻይና፣ ህንድ፣ ብራዚል እና ደቡብ አፍሪካ ህብረት የሆነው ብሪክስ ፕሬዝዳንት ፑርኒማ አናንድ እንደገለጹት በአባል ሀገራቱ መካከል የዶላር ግብይት አያስፈልግም ብለዋል።
እንደ ራሺያ ቱዴይ ዘገባ ከሆነ ሩሲያ እና ህንድ ለሚያደርጓቸው የእርስ በርስ ንግድ ልውውጥ ሩብል እና ሩፒን ለመጠቀም መስማማታቸውን ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል ።
ሁለቱ ሀገራት ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ጦርነት መክፈቷን ተከትሎ በአሜሪካ እና አውሮፓ ህብረት ማዕቀብ በመጣሉ ነው።
በመሆኑም ሩሲያ እና ህንድ ይሄ ማዕቀብ ለንግዳቸው እንቅፋት እንዳይሆን በሚል የየራሳቸው መገበያያ ገንዘብ ለመጠቀም መወሰናቸው ተገልጿል።
ሕንድ በዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት ጉዳይ ላይ ገለልተኛ አቋም እንደምታራምድ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ የአሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ማዕቀቦች በሩሲያ ላይ በተጨመሩ ቁጥር ህንድ ከሞስኮ ጋር የምታደርጋቸው ትብብሮች ይጨምራልም ብለዋል።
ሕንድ ከሩሲያ ነዳጅ እንዳትገዛ ከአሜሪካ ተጽዕኖ ሲደርስባት የቆየ ሲሆን የህንድ ውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ጥያቄውን ውድቅ ማድረጉ ተጠቅሷል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከሩሲያ ጋር ቀጥታ ጦርነት ውስጥ ላለችው ዩክሬን ተጨማሪ የሶስት ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው የጦር መሳሪያ ድጋፍ ከሰሞኑ መፈረማቸው ይታወሳል።
አሜሪካ የጦር መሳሪያውን ድጋፍ ያደረገችው ዩክሬን የኑክሌር ጥቃት ከሩሲያ ሊያጋጥማት ይችላል በሚል እንደሆነ ሮይተርስ ዘግቧል።የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ 184ኛ ቀኑ ላይ ሲገኝ ከ10 ሚሊዮን በላይ ዩክሬናዊያን ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል።