ሩሲያ እና ቻይና፤ የቡድን 7 ሀገራት “አለምን በሁለት ጎራ ለመክፈል እየሰሩ ነው” አሉ
የቡድን 7 አባል ሀገራት በጃፓን ሄሮሺማ ባደረጉት ስብሰባ በሞስኮ እና ቤጂንግ ላይ ያነጣጠሩ ውሳኔዎችን አሳልፈዋል
የመንግስታቱ ድርጅትም የቡድን ሰባት ሀገራት እና የቻይና ፍጥጫ የቀዝቃዛው ጦርነት አይነት የሀገራት ጎራ መለየትን እንዳይፈጥር አሳስቧል
ሩሲያ እና ቻይና የቡድን 7 አባል ሀገራት ትናንት በጃፓኗ ሄሮሺማ ባደረጉት ስብሰባ ያሳለፉት ውሳኔ “ሀገራቱን ለማፈን” ያለመ ነው በሚል ተቃውመውታል።
የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ፥ “ምዕራባውያን ዩክሬንን በሩሲያ ላይ ስትራቴጂካዊ ድል ለመቀዳጀት እየተጠቀሙባት ነው” ብለዋል።
“ሩሲያን በአውደ ውጊያ በማሸነፍ የጂኦፖለቲካ ተፎካካሪያቸውን የማጥፋት ግባቸውንም በግልጽ ሲናገሩ አይተናል” ነው ያሉት ላቭሮቭ ከሀገሪቱ ብሄራዊ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ።
የቡድን 7 አባል ሀገራት በሄሮሺማው ስብሰባ ሀገራት ከሩሲያ ጋር የንግድ ግንኙነታቸውን እንዲያቆሙና የተለያዩ ማዕቀቦችን ለመጣል ቢዝቱም “ሞስኮ ብዙ ወዳጆች አሏት” ብለዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ።
የሩሲያ ዋነኛ አጋር ቻይናም በትናንቱ ጉባኤ ትኩረት የተደረገባት ሀገር ናት።
ቻይና በደቡብ ቻይና ባህር እያደረገች ያለውን “ወታደራዊ መስፋፋት” እንድታቆም ያሳሰቡት የቡድን 7 አባል ሀገራት፥ በታይዋን ጉዳይም “አቋማችን የጸና ነው” የሚል መግለጫቸውን አውጥተዋል።
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫም፥ የቡድን ሰባት አባል ሀገራት የሄሮሺማውን ስብሰባ “ቻይናን ለማጥቃትና በውስጥ ጉዳዩዋ ላይ ጣልቃለመግባት ተጠቅመውበታል” ሲል ተቃውሞውን አሰምቷል።
ቤጂንግ የግዛቴ አካል ናት በምትላት የታይዋን ደሴት ዙሪያ የሚነሱ ጉዳዮች ላይ ሀገራቱ የሚሰጡትን አስተያየት ግልጽ ጣልቃገብነት አድርጋ እንደምትመለከተውም መግለጫው ማመላከቱን ሬውተርስ አስነብቧል።
“ቻይና አለም አቀፍ ህጎችን እየጣሰች ነው” በሚል ለቀረበባት ክስም፥ “ቻይና የመንግስታቱ ድርጅት የሚመራውን አለምአቀፍ ስርአት ትከተላለች፤ ይሁን እንጂ ጥቂቶች የሚያወጡትን ህግ አትቀበልም” የሚል ምላሽ ሰጥታለች።
“ምዕራባውያን ብቻ የተሰባሰቡበት የቡድን 7 አባል ሀገራት የሚያወጡትንና አለምን የሚከፋፍል ህግና ስርአት አለማቀፉ ማህበረሰብ ሊቀበል አይችልም” ሲልም ነው የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የገለጸው።
ሩሲያ እና ቻይና የትናንቱን የቡድን 7 አባል ሀገራት ውሳኔ ሞስኮ እና ቤጂንግን “ለማፈን” የተደረገ መሆኑን ያምናሉ።
ሀገራቱ የያዙት አቋም አሜሪካ እና ወዳጆቿን በአንድ ወገን ፤ ቻይና እና ሩሲያን ደግሞ በሌላ ጎራ የሚያሰልፍ የቀዝቃዛው ጦርነት አይነት አሰላለፍን ይፈጥራል የሚል ስጋት አጭሯል።
የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝም ምዕራባውያን ከቻይና ጋር የገቡበት ፍጥጫ አለምን በሁለት ጎራ መክፈሉ እንደማይቀር ነው የገለጹት።
ሀገራቱ በኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ እና ወታደራዊ ጉዳዮች ያሏቸውን ልዩነቶች በፍጥነት በንግግር ካለፈቱ የተፈራው አይቀርም ሲሉ ማሳሰባቸውንም የጃፓኑ ኪዮዶ ኒውስ ዘግቧል።