ዩክሬን 6 የሩሲያ ሃይፐርሶኒክ ሚሳይሎችን መትታ መጣሏን አስታወቀች
ሩሲያ በበኩሏ “ኪንዝሃል” የተሰኙት ሚሳይሎች የአሜሪካን ሚሳኤል መቃወሚያ ከጥቅም ውጭ ማድረጋቸውንና ተመተው አለመውደቃቸውን ገልጻለች
አሜሪካ ከድምጽ አምስት እጥፍ የሚፈጥኑት ሚሳኤሎች ስለመመታታቸው አላረጋገጠችም
ዩክሬን በትናንትናው እለት ስድስት የሩሲያ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎችን መጣሏን አስታውቃለች።
የሀገሪቱ ጦር ኢታማዦር ሹም ቫለሪ ዛሉዥኒ እንደገለጹት፥ ከአውሮፕላን ላይ የተተኮሱት ስድስት “ኪንዝሃል” ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎች ተመተው ወድቀዋል።
ከዚህም ባሻገር ከጥቁር ባህር ከመርከብ ላይ የተተኮሱ ዘጠኝ ክሩዝ ሚሳኤሎችን ማክሸፍ መቻሉን ተናግረዋል።
የሩሲያው መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌ ሾጉ በበኩላቸው፥ የኬቭን መረጃ ውድቅ አድርገዋል።
ኪንዝሃል ሚሳይሎቹ በኬቭ የሚገኘውን አሜሪካ ሰራሽ የጸረ ሚሳኤል ስርአት (ፓትሪዮቲክ ሲስተም) ከጥቅም ውጭ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ሮይተርስ ሁለት የአሜሪካ ባለስልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው የሚሳኤል መቃወሚያ ስርአቱ ጉዳት ያስተናገደ ሲሆን፥ ሰርጌ ሾጉ እንዳሉት ግን ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጭ አልሆነም።
ፔንታጎን ግን ስለጉዳዩ የሰጠው ምላሽ የለም።
የሩሲያው መከላከያ ሚኒስትር “ኬቭ መትቼ ጥያቸዋለሁ ያለቻቸው ሚሳኤሎች ቁጥር ከተኮስነው በሶስት እጥፍ የሚልቅ ነው፤ የተኮስነውን ሚሳኤል አይነትም በውል አላወቁትም፤ ለዚያም ነው ሊመቷቸው የማይችሉት” የሚል ምላሽ መስጠታቸውንም ነው አርቲ ያስነበበው።
ዩክሬን የሩሲያን ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል መትቻለሁ ስትል የትናንቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ኬቭ በትክክልም ኪንዝሃል ሚሳኤሎችን ከመታች ከምዕራባውያኑ ያገኘችው የጸረ ሚሳኤል መቃወሚያ ስርአት ውጤታማነትን ያሳያል ተብሏል።
ፕሬዝዳንት ቮልድሚር ዜለንስኪም “ከአመት በፊት ሚሳኤሎችን በተለይ ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤሎችን መተን የመጣል አቅም አልነበረንም” ሲሉ የምዕራባውያኑ ድጋፍ እንዲቀጥል በአይስላንድ ለተሰባሰቡ የአውሮፓ ሀገራት ጥሪ አቅርበዋል።
ሞስኮ በበኩሏ ምዕራባውያኑ ለዩክሬን የሰጧቸው መሳሪያዎች የተከማቹባቸውን ስፍራዎች ኢላማ ያደረጉ የሚሳኤል ጥቃቶችን አጠናክራ እንደምትቀጥል ነው በመከላከያ ሚኒስትሯ በኩል ያስታወቀችው።