ሩሲያ ሳይንቲስቶቹን የጠረጠረችው ከሰሞኑ ወደ ዩክሬን የተተኮሰው ኪንዛል ሚሳኤል መመታቱን ተከትሎ ነው
ሩሲያ ሶስት ሳይንቲስቶችን በሀገር ክህደት ከሰሰች።
ከዩክሬን እና ደጋፊዎቿ ጋር እየተዋጋች ያለችው ሩሲያ ከሰሞኑ ለየት ያሉ ሚሳኤሎችን በመተኮስ ላይ ትገኛለች።
በተለይም ኪንዛል ሀይፐር ሶኒክ ሚሳኤል የተሰኘው ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የዩክሬን የጦር መሳሪያ መጋዝን እና ሌሎች የቴክኖሎጂ ማዕከላትን እንዳወደመችበት ተገልጿል።
በአሜሪካ ለረጅም ዓመታት እንደተገነባ የተገለጸው እና በዩክሬን ዋና ከተማ ኪቭ የሚገኘው የጸረ ሚሳኤል ማዕከል ኪንዛል በተሰኘው ባልስቲክ ሚሳኤል መውድሙ ተረጋግጧል።
ይሁንና ዩክሬን ከሩሲያ የተተኮሰውን ኪንዛል ሚሳኤልን መትታ መጣሏ ሲገለጽ ሞስኮ ይህ እንዴት ሆነ ስትል ፊቷን ወደ ሳይንቲስቶቿ አዙራለች።
እንደ ሮይተርስ ዘገባ በዚህ ዘመናዊ ሚሳኤል ምርት የተሳተፉ ሶስት ሳይንቲስቶች የሀገር ሚስጢሮችን ለጠላት አሳልፈው ሳይሰጡ እንዳልቀሩ ተጠርጥረዋል።
በሳይንቲስቶቹ ላይ ምርመራ መጀመሩን ተከትሎም በሩሲያ የተመራማሪዎች ማህበረሰብ ላይ ድንጋጤን ፈጥሯል ተብሏል።
የሳይቤሪያ ሳይንቲስት ማህበር በሳይንቲስቶቹ ላይ የተጀመረውን ምርመራ የተቃወመ ሲሆን የሩሲያ መንግሥት ግን ጉዳዩ የሀገር ደህንነት ጉዳይ ነው ሲል ምላሽ መስጠቱ ተገልጿል።
በሀገር ክህደት ወንጀል የተጠረጠሩት ሳይንቲስቶች ድርጊቱን የተቃወሙ ሲሆን ምርመራው የሩሲያን ሳይንስ ይጎዳል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሞስኮ በሀይፐር ሶኒክ ሚሳኤል ቴክኖሎጂ የዓለም መሪ መሆኗን ገልጸዋል።