ሩሲያ ከብሪታንያ ለዩክሬን በተሰጠ ሚሳኤል ጥቃት እንደተፈጸመባት ተናገረች
ብሪታንያ ለኪየቭን የረጅም ርቀት ሚሳይሎችን ማቅረቧን የተናገረች የመጀመሪያዋ ሀገር ሆናለች
ሚሳይሎቹ በዩክሬን ግዛት እንጅ በዓለም አቀፍ ድንበር ውስጥ ጥቅም ላይ እንደማይሉ ማረጋገጫ ከኪየቭ መሰጠቱ ተነግሯል
ሩሲያ ከብሪታንያ ለዩክሬን በተሰጠ የረጅም ርቀት ሚሳኤል ጥቃት እንደተፈጸመባት ተናገረች።
የሩሲያ መከላከያ ሚንስቴር እንዳስታወቀው የዩክሬን አውሮፕላኖች ከብሪታኒያ በቀረበላቸው የረዥም ርቀት ሚሳይሎች በሩሲያ ቁጥጥር ስር በምትገኘው ሉሃንስክ ከተማ ሁለት የኢንዱስትሪ ቦታዎችን ደብድበዋል።
ብሪታንያ ሀሙስ ዕለት ለኪየቭ የረዥም ርቀት የመርከብ ሚሳይሎችን ማቅረብ መጀመሯን የተናገረች ሲሆን ይህም ለከፍተኛ የመልሶ ማጥቃት መዘጋጀትን ያስችላታል ተብሏል።
የብሪታኒያ የመከላከያ ሚንስትር ቤን ዋላስ ሚሳይሎቹ በዩክሬን ግዛት ውስጥ ጥቅም ላይ ሊዉሉ እንደሚችሉ በመግለጽ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ባለው ሩሲያ ድንበሮች ውስጥ ኢላማዎችን ለማጥቃት እንደማይጠቀሙበት ከኪየቭ ማረጋገጫ እንደደረሳቸው ተናግረዋል።
"በብሪታንያ ለኪየቭ አገዛዝ የተሰጡ ከአየር ወደ አየር የሚወነጨፉ ሚሳይሎች ለጥቃቱ ጥቅም ላይ ውለዋል። ይህም የጦር መሳሪያዎቹ በሲቪል ኢላማዎች ላይ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ለንደን ከተናገረችው በተቃራኒው ነው" ሲል የሩሲያ መከላከያ ሚንስቴር ተናግሯል።
በተጨማሪም ሩሲያ ሚሳኤሎቹን ያስወነጨፉትን ሁለት የዩክሬን የጦር አውሮፕላኖች ሱ-24 እና ማይግ-29 መታ መጣሏን ተናግራለች።
ሚኒስቴሩ በቅርቡ ባወጣው መግለጫ የሩሲያ ጦር በምስራቅ ባክሙት ከተማ የሚገኝ ስፍራ መቆጣጠሩን ገልጿል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል።