ቻይና እና አሜሪካ “በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ያልተጠበቀ ስምምነት” አደረጉ
የአሜሪካ “በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ አብሮ ከመስራት ውጭ ሌላ አማራጭ የለንም” ብላለች
ቻይና በበኩሏ “በአየር ንብረት ለውጥ ከሚያለያየን ይልቅ የምንስማማበት ይበዛል” ስትል ተናግራለች
በበርካታ የዓለማችን አንኳር ጉዳዮች ላይ የተለያዩ አቋሞች ሲያራምዱ የሚስተዋሉት ቻይና እና አሜሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ያልተጠበቀ ስምምነት ማድረጋቸው ተሰምቷል።
በስኮትላንዷ ግላስጎው ከተማ እየተካሄደ ባለው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በመሳተፍ ላይ የሚገኙትና ካርበንን በመልቀቅ ሀገራት ከፍተኛ ድርሻ እንደሚይዙ የሚነገርላቸው ሀገራቱ “በቀጣይ 10 ዓመታት ለውጥ ያመጣል የተባለለትን ስምምነት” ይፋ አድርገዋል።
ሀገራቱ ለአየር ንብረት ለውጥ ዋነኛ ምክንያት የሆኑቱን “የሚቴን እና የካርቦን ልቀት ለመቀነስ” መስማማታቸውንም ነው የገለጹት።
ቻይና ባለፈው ሳምንት “የሚቴን ጋዝ ለመቀነስ ፈቃደኛ አይደለሁም” ማለቷን ተከትሎ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከፍተኛ ድንጋጤ ፈጥሮ የነበረ ቢሆኑም፤ በዚሁ ስምምነት ውሳኔዋን መቀየሯ ተነግሯል።
በዚሁ ስምምነት ሁለቱም የዓለማችን ኃያላን እንደፈረንጆቹ በ2015 የተደረሰውንና የሙቀት መጠኑ ከ1.5 ዲግሪ ሴንትግሬድ በላይ እንዳይሆን የሚያችል ‘የፓሪስ ስምምነት’ በማክበር ለተግባራዊነቱ እንደሚሰሩም ለመጀመርያ ጊዜ ቃል ገብተዋል።
የምድራችን የሙቀት መጠን ወደ 1.5 ዲግሪ ሴንትግሬድ ዝቅ እንዲል ማድረግ በአየር ለውጥ ምክንያት በሰብዓዊነት ላይ ሊደርስ የሚችለው አደጋ ለምግታት እንደሚያስችል የዘርፉ ተመራማሪዎች በተለያዩ ጊዜያት ስገልጹ ይስተዋላል።
እንደፈረንጆቹ በ2015 በፓሪሱ ጉባኤ፤ የዓለም መሪዎች የሙቀት መጠኑ በ1.5 እና 2 ዲግሪ ሴንትግሬድ እንዲወሰን ከስምምነት መድረሳቸው የሚታወስ ነው።
የቻይና ከፍተኛ ተደራዳሪ ዢ ዤንዋ፤ በአየር ንብረት ለውጥ ቻይና እና አሜሪካ ከሚለያያቸው ይልቅ የሚስማሙበት እንደሚበዛ ተናግረዋል።
በአየር ንብረት ጉዳዮች ዙርያ የአሜሪካው ዋና ተደራዳሪ ጆን ኬሪ “አሜሪካ እና ቻይና ብዙ የሚለያዩበት አጀንዳ አለ፤ በአየር ንብረት ጉዳይ ግን አብሮ በመስራት ብቻ ለውጥ እንደሚመጣ ያውቃሉ” ብለዋል።
ጆን ኬሪ አክለውም "እያንዳንዱ እርምጃችን ወሳኝ ነው፤ በቀጣይም ረዥም ጉዞ ይጠብቀናል" ሲሉ ተናግረዋል።
የአሜሪካው ፐሬዚዳንት ጀ ባይደን እና የቻይና አቻቸው ዢ ጂንፒንግን በቀጣይ ሳምንት የበይነ መረብ [ቪርቹታል] ስብስባ ያደርጋሉም ነው የተባለው።
በግላስጎው እየተካሄደ ባለ የCOP-26 ጉባኤ የመጨረሻ የተባለለት ረቂቅ ሰነድ ለፊርማ ተዘጋጅቶ እንደሚገኝ መሪጃዎች ይጠቁማሉ።