ያደጉ ሃገራት ለአዳጊ ሃገራት ለመስጠት ቃል የገቡትን 100 ቢሊዮን ዶላር እንዲሰጡ ተጠየቀ
በ2009ኙ የኮፐን ሃገን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይ ነበር ለተጎጂ ሃገራት በየዓመቱ የ100 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ ቃል የተገባው
ሃገራቱ በፈረንጆ 2020 እናደርገዋለን ብለው ከ10 ዓመት በፊት የገቡትን ቃል እንዲያከብሩ ተጠይቋል
የአየር ንብረት ለውጥ ገፈትን ቀማሽ ለሆኑ አዳጊ ሃገራት ቃል የተገባው የድጋፍ ገንዘብ እንዲሰጥ ተጠየቀ፡፡
ይህ የተጠየቀው በስኮትላንድ ግላስኮው በመካሄድ ላይ ባለው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ (ኮፕ26) ላይ ነው፡፡
በጉባዔው በመሳተፍ ላይ የሚገኙ አዳጊ ሃገራት በልጽገናል የሚሉ ሃገራት በየዓመቱ ለመስጠት ቃል የገቡትን 100 ቢሊዮን ዶላር እንዲሰጡ ጠይቀዋል፡፡
በጉባዔው ጥያቄውን ካቀረቡ ሃገራት መካከል አንዷ ኬንያ ነች፡፡ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያ በጉባዔው መክፈቻ ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል፡፡
ሃገራቱ ቃላቸውን እንዲያከብሩ የጠየቁት የአካባቢ እና ደን ሚኒስትሯ ኬሪያኮ ቶቢኮም የጉባዔው ተሳታፊ ናቸው፡፡
ኢትዮጵያ በፕ/ር ፍቃዱ በየነ በተመራ ቡድን ተወክላ በጉባዔው በመሳተፍ ላይ ትገኛለች
“ከ10 ዓመት በፊት ቃል ስለተገባው 100 ቢሊዮን ዶላር እንደሰማችሁ እርግጠኛ ነኝ፡፡ በባለፈው ዓመት ለመስጠት ነበር ቃል የተገባው፤ ሆኖም ያ አልሆነም” ነው ኬሪያኮ ቶቢኮ ያሉት፡፡
ሚኒስትሩ የበለጸጉት ሃገራት ኬንያን ጨምሮ ሌሎችንም ሃገራት ከአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖዎች ለመጠበቅ በ2015ቱ የአየር የአየር ንብረት ስምምነት ወቅት የገቡትን ቃል እንዲያከብሩም ጠይቀዋል፡፡
ሃገራቱ ቀዳሚ በካይ ጋዝን ለቃቂዎች መሆናቸውን በማስታወስ የዚህን ገፈት አፍሪካ ቀድማ እየቀመሰችም ነው ብለዋል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ በምስራቅ አፍሪካ ብቻ በ10 ሚሊየን ሰዎችን ሊያፈናቅል ይችላል- የዓለም ባንክ
ለዚህም ሃገራቸው ሁልጊዜ ድርቅና ሌሎች ተጽዕኖዎችን በተመለከቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ስር መሆኗን ነው ኬሪያኮ የተናገሩት፡፡
በልጽገናል የሚሉ ሃገራት በ2009ኙ የኮፐን ሃገን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይ ነበር ለተጎጂ ሃገራት በየዓመቱ የ100 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ እናደርጋለን በሚል ቃል የገቡት፡፡ ቃሉ በፓሪሱ የአየር ንብረት ጉባዔም ወቅት በ2021 እንደሚተገበር ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ሆኖም በተለያዩ ምክንያቶች ቃሉ ተፈጻሚ ሳይሆን ቀርቷል፡፡
ይህ መሆኑ ተቀባይነት እንደሌለው ከአል ዐይን አማርኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ የገለጹት የአፍሪካ ህብረት የግብርና ገጠር ልማት፣ ብሉ ኢኮኖሚና ዘላቂ ከባቢ አየር ኮሚሽነር አምባሳደር ጆሴፋ ሳኮ አፍሪካ በምግብ ራሷን ለመቻል በምታደርገው ጥረት “የአየር ንብረት ለውጥ ዋነኛ ፈተና” መሆኑን ተናግረዋል፡፡