ከ40 በላይ ሀገራት የድንጋይ ክሰልን መጠቀም ለማቆም ቃል ገቡ
በድንጋይ ክሰል ላይ ጥገኛ የሆኑት ቻይና፣ አውስትራሊያ፣ ህንድና አሜሪካ ቃልኪዳኑን አለመፈረማቸው ተሰምቷል
በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ባንኮችም ለድንጋይ ክሰል እንዱስትሪዎች ፋይናንስ ማቅረብ ለማቆም ተስማምተዋል
ከ40 በላይ ሀገራት በግላሶኮ እየተካሄደ ባለው የኮፕ26 የአየር ንብረት ጉባዔ ላይ የድንጋይ ክሰልን መጠቀም ለማቆም ቃል መግባታቸውን የብሪታኒያ መንግስት አስታወቀ።
ቃል ከገቡ ሀገራት መካከልም የድንጋይ ክሰልን በከፍተኛ ደረጃ የሚጠቀሙ ሀገራት ማለትም ፖላንድ፣ ቬትናማ እና ቺሊ የሚገኙበት መሆኑም ተነግሯል።
የቃል ኪዳን ስምምነቱን የፈረሙት ሀገራት ከድንጋይ ክሰል ጋር ተያይዞ በሀገር ውስጥ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ኢንቨስትመንቶችን የሚያቋርጡ መሆኑም ተነግሯል።
በፈረንጆቹ 2030ም ከድንጋይ ክሰል ከሚያገኙት የኃይል አማራጭ ለመውጣጥ ቃል መግባታቸውም ታውቋል።
በተጨማሪም በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት የቃል ኪዳን ስምምነቱን መፈረማቸው የተነገረ ሲሆን፤ በርካታ ባንኮችም ለድንጋይ ክሰል እንዱትሪዎች ፋይናንስ ማቅረብ ለማቆም መስማማታቸው ተነግሯል
ሆኖም ግን በድንጋይ ክሰል ላይ ጥገኛ የሆኑ እንደ ቻይና፣ አውስትራሊያ፣ ህንድ፣ እና አሜሪካ ቃልኪዳኑን አለመፈረማቸው ተሰምቷል።
እንደ ፈረንጆቹ በ2019 በተሰራ ጥናት ከዓለምችን የኤሌክትሪክ ምንጮች ውስጥ የድንጋይ ክሰል 37 በመቶውን እንደሚይዝ ያመላክታል።
ይሁን እንጂ የድንጋይ ክሰል በዓለም የአየር ንብረት ለውጥ እንዲከሰት ከፍተኛውን ሚና የሚጫወት እንደሆነም ነው የሚነገረው።