ዩኤኢና አሜሪካ በ4 ቢልየን ዶላር የሚገመት "የግብርና ፈጠራ ለአየር ንብረት" ኢንሼቲቭ ጀመሩ
ኢንሼቲቩ ከ2 ቢሊየን በላይ ለሚሆኑ የዓለማችን ሰዎች የስራ እድሎችን የሚፈጥር ነው ተብሏል
ዩኤኢ በ6 አህጉራት በሚገነቡ የታዳሽ ኃይል ልማት ፕሮጄክቶች ላይ 17 ቢሊየን ዶላር ገደማ ገንዘብን ፈሰስ ማድረጓ ይታወቃል
የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች (ዩኤኢ) እና ዩናይትድ ስቴትስ በ4 ቢልየን ዶላር የሚገመት "የግብርና ፈጠራ ለአየር ንብረት" ኢንሼቲቭ መጀመራቸውን አስታወቁ።
የአየር ንብረት ፈጠራ ኢንሼቲቩ ይፋ ያደረጉት 30 ሀገራት እየተሳተፉበት ባለና በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ላይ እየመከረ በሚገኘው COP-26 ላይ ነው።
በ4 ቢሊየን ዶላር የሚጀመረው ኢንሼቲቭ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ፤ ከአየር ንብረት ጋር የሚስማማ-ዘመናዊ የምግብ እና የግብርና ሥርዓቶችን የማስፋፋት ሥራን ለማፋጠን ያለመ ነው።
ዩኤኢ የጅምሩ አካል የሆነ ተጨማሪ 1 ቢሊየን ዶላር ኢንቨስትመንት ለመስጠትም ቃል ገብታለች።
ኢንሼቲቩ የግብርናውን ሴክተር ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅዖ የሚያጎላብት እና በዚህ ወሳኝ ሴክተር ውስጥ ከ2 ቢሊየን በላይ ለሚሆኑ የዓለማችን ሰዎች የስራ እድሎችን የሚፈጥር ነው ተብሏል።
በአየር ንብረት ለውጥ የዩኤኢ ልዩ መልዕክተኛ፣ የኢንዲስትሪ እና የላቀ ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር ሱልጣም ቢን አህመድ አል-ጃባር "ከአስተዋይ አመራር ራዕይ ጋር በተጣጣመ መልኩ ዩኤኢ ለአየር ንብረት ለውጥ መዘዞች ተግባራዊ መፍትሄዎችን በማፈላለግ እና ኢኮኖሚያዊ እድሎችን በመፍጠር ላይ ትኩረት አድርጋ በመስራት ላይ ናት፤ ይህን ኢንሼቲቭ በመጀመራችን ደስተኞች ነን" ብለዋል።
ዩኤኢ 17 ቢሊየን ዶላር የሚጠጋ ለታዳሽ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች የሚሆን መዋዕለ ንዋይ ማፍሰሷ በኢነርጂው ዘርፍ ለሚደረገው የለውጥ ምዕራፍ ዝግጅት፣ ለፈጠራ እና ለአረንጓዴ ልማት ትኩረት በመስጠት ፈር ቀዳጅ እንደሚያደርጋትም ነው ሚኒስትሩ ያነሱት።
በአየር ንብረት ለውጡ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ልዩ መልዕክተኛ ጆን ኬሪ በበኩላቸው “አሜሪካ ከዩኤኢ እና 80 የሚሆኑ አጋሮች ጋር በመሆን ኢንሼቲቩን መጀመሯ ኩራት ይሰማታል።
ኢንሼቲቩ የአየር ንብረት ቀውሱን ለመቅረፍ ወሳኝ እንደሆነ እናስባለን; ይህም የካርበን ልቀትን ለመቀነስ፣ እያደገ የመጣውን የዓለም ህዝብ የምግብ ፍላጎት ለማሟላት እና አርሶ አደሮች እና አርቢዎች የአየር ንብረት ለውጥን ተፅእኖ እንዲለማመዱ ለመርዳት የሚያስችል ነው” ሲሉ ተናግሯል።
የ"ግብርና ፈጠራ ለአየር ንብረት" የተሰኘ ኢንሼቲቩ አዘርባጃን፣ካናዳ እና እንግሊዝን ጨምሮ በ30 ሀገራት እና 48 የግል ድርጅቶች ድጋፍ ማግኘቱንም ነው የተገለጸው።