ቻይና ከቀናት በፊት ህይወታቸው ያለፈውን ንግስት ኤልሳቤት አስከሬን እንዳትጎበኝ ታገደች
ብሪታንያ የቻይና ዲፕሎማቶች ሀዘናቸውን ለመግለጽ ወደ ምክር ቤት እንዳይገቡ አግዳለች
እገዳው የተጣለው በሁለቱ ሀገራት የዲፕሎማሲ ውጥረት ምክንያት ነው ተብሏል
ቻይና ከቀናት በፊት ህይወታቸው ያለፈውን ንግስት ኤልሳቤት አስከሬን እንዳትጎበኝ ታገደች።
ብሪታንያን ላለፉት 70 ዓመታት በንግስትነት ያገለገሉት ንግስት ኤልሳቤት በ96 ዓመታቸው ማለፉ ይታወሳል።
በርካታ የአለማችን ሀገራት በንግስቲቱ ሞት ሀዘናቸውን በመግለጽ ላይ ይገኛል።
የንግስት ኤልሳቤት አስከሬን በብሪታንያ የተለያዩ ቦታዎች እየተዘዋወረ እና ዜጎችም ሀዘናቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።
የንግስት ኤልሳቤት አስከሬን ከትናንት ጀምሮም በሀገሪቱ ህግ አውጪ ምክር ቤት የተቀመጠ ሲሆን ስርዓተ ቀብሩ እስከሚፈጸም ድረስ ይቆያል ተብሏል።
ይሄንን ተከትሎም በብሪታንያ ያሉ የተለያዩ የዓለማችን ሀገራት ተወካዮች በምክር ቤቱ እየገቡ ሀዘናቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው።
በለንደን ያለው የቻይና አምባሳደር ሀዘናቸውን ለመግለጽ ቢሞክሩም ተከልክለው እንደተመለሱ ቢቢሲ ዘግቧል።
እንደ ዘገባው ከሆነ የቻይና ዲፕሎማቶች ሀዘናቸውን ለመግለጽ እንዳይገቡ የተከለከሉት በብሪታንያ እና ቻይና የዲፕሎማሲ ውጥረት ምክንያት ነው ተብሏል ።
ቻይና ባሳለፍነው ዓመት ከኡጉር ሙስሊም እምነት ተከታዮች ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ዙሪያ በብሪታንያ ምክር ቤት አባላት እና ፖለቲከኞች ላይ ማዕቀብ ጥላ ነበር።
ብሪታንያም በቻይና ለተጣለባት ማዕቀብ ተመሳሳይ ምላሽ ባትሰጥም በህግ አውጪ ምክር ቤት አባላት ላይ ማዕቀብ የተጣለብን አምባሳደር ወደ ምክር ቤቱ አዳራሽ ሊገባ አይችልም በሚል እገዳ ጥላለች።
ይሁንና ብሪታንያ ለቻይና ፕሬዝዳንት ሺ ዢ ፒንግ የፊታችን ሰኞ በሚካሄደው የንግስት ኤልሳቤት ስርዓተ ቀብር ላይ እንዲገኙ ጋብዛለች።
ፕሬዝዳንቱ ግብዣውን ተቀብለው ወደ ለንደን ይመጣሉ ተብሎ ባይጠበቅም ተወካይ እንደሚልኩ ይጠበቃል።
የንግስት ኤልሳቤት ህልፈተ ህይወትን ተከትሎ የንግስቲቱ የበኩር ልጅ የሆኑት ልዑል ቻርልስ የብሪታንያ ንጉስ ሆነው መሾማቸው ይታወሳል።