ቻይና በናንሲ ፔሎሲ እና ቤተሰቦቻቸው ናይ ማዕቀብ መጣሏ ይታወሳል
ቻይና ከአሜሪካ ጋር ወታደራዊ ትብብሯን ማቋረጧን አስታውቃለች።
ታይዋንን የጎበኙት የአሜሪካ አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ በአሜሪካ እና ቻይና ግንኙነት ላይ ትልቅ አስተዋጽኦን በመጫወት ላይ ይገኛል።
ቻይና በናንሲ ፔሎሲ የታይዋን ጉብኝት ክፉኛ መበሳጨቷን ያሳወቀች ሲሆን በእስያ ፖለቲካ ውስጥ ትልቅ ለውጦችን ማምጣት የሚያስችሉ ውሳኔዎች በመተላለፍ ላይ ናቸው።
ቻይና ከሰሞኑ በታይዋን ስድስት አቅጣጫ የአየር፣ ባህር እና ሌሎች አይነት ወታደራዊ ልምምድ በማድረግ ላይ ትገኛለች።
አሁን ደግሞ ቻይና ከአሜሪካ ጋር ወታደራዊ ትብብሮችን ማቋረጧን ያሳወቀች ሲሆን ተጨማሪ ውሳኔዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ሮይተርስ ዘግቧል።
ቻይና እስካሁን ከከፍተኛ ወታደራዊ ትብብሮች ባለፈ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ከዚህ በፊት የነበራትን የከፍተኛ መሪዎች የጋራ ውይይት መድረኮችን ከአሜሪካ ጋር ላለማድረግ መወሰኗን በውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ በኩል አሳውቃለች።
እንዲሁም ቻይና ከአሜሪካ ጋር የነበራትን የድንበር አልባ ወንጀል መከላከል፣ ስደተኞችን ማጓጓዝ፣ አደገኛ እጽ ዝውውር መከላከል እና ሌሎች ስምንት የትብብር መስኮችን አቋርጣለች።
ቻይና ሰሞኑን ታይዋንን በጎበኙት የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ላይ ማዕቀብ መጣሏ ይታወሳል፡፡
የቻይና ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል ቀባይ ጽ/ቤት፤ ሀገሪቱ በናንሲ ፔሎሲ እና በቤተሰቦቻቸው ላይ ማዕቀብ መጣሏን ሲጂቲኤን ዘግቧል።
ናንሲ ፔሎሲ በእስያ ጉብኝታቸው ታይዋንን ጎብኝተው ነበር፡፡
በአፈጉባዔዋ ጉብኝት የተቆጣችው ቤጅንግ፤ የአንድ ቻይና ፖሊሲ መርህ አንደተጣሰ እና ለዚህም አጸፋዊ ምላሽ እንደምትሰጥ ስትዝት ቆይታለች፡፡
እስካሁን ባለው ሁኔታ ከ30 በላይ የቻይና ተዋጊ ጀቶች የታይዋንን ሰማይ አቋርጠው ገብተዋል፡፡
በአንድ ቀን ብቻ 27 የቻይና የጦር አውሮፕላኖች በታይዋን ሰማይ መብረራቸውን ቻይናም ታይዋንም ሲገለጹ ነበር፡፡
ቻይናን፤ በታይዋን ዙሪያ ወታደራዊ ልምምድ እያደረገች ሲሆን የሚሳኤል ተኩስም ማድረጓን መግለጿ ይታወሳል፡፡
ቻይና፤ የአሜሪካ አፈጉባዔ ታይዋንን በመጎብኘታቸው ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እርምጃ ልትወስድ እንደምትችል አስጠንቅቃ የነበረ ሲሆን ዛሬም በአሜሪካ እና ታይዋን ላይ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ትገኛለች።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና አውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ሀገራትና ተቋማት በአንድ ቻይናን ፖሊሲ እንደሚያምኑ አስታውቀዋል፡፡
የአንድ ቻይና ፖሊሲ፤ ታይዋን፤ በቻይና መንግስት ስር እንደሆነችና የቻይና ሉዓላዊ ግዛት አካል እንደሆነች የሚያረጋግጥ መርህ ነው፡፡