ከአሜሪካ-ቻይና ትብብር ውጭ የዓለም ታላላቅ ችግሮችን መፍታት አይቻልም - አንቶኒዮ ጉቴሬዝ
የናንሲ ፔሎሲ የታይዋን ጉብኝት በአሜሪካ እና ቻይና ግንኙነት ላይ ትልቅ አስተዋጽኦን በመጫወት ላይ ይገኛል
ቻይና ከአሜሪካ ጋር የምታደርገው ወታደራዊ ትብብር ማቋረጧ አይዘነጋም
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ዋና ኃላፊ ከአሜሪካ-ቻይና ትብብር ውጭ የዓለም አቀፍ ቁልፍ ጉዳዮችን ለመፍታት የሚደረግ 'ምንም መንገድ የለም' ብለው እንደሚያምኑየዋና ጸሃፊው ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪች ተናገሩ ።
ቃል አቀባዩ ይህን ያሉት ፤ ቻይና ከአየር ንብረት እስከ ወታደራዊ ንግግሮች ባሉ በርካታ ጉዳዮች ላይ ከአሜሪካ ጋር ትብብሯን ለማቆም መወሰኗን አስመልክቶ የተመድ አስተያየትና እምነት ምን ሊሆን ይችላል በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምልሽ ነው፡፡
ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪች ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በአሜሪካ እና በቻይና መካከል ትብብር ከሌለ “የዓለምን ታላላቅ ተግዳሮቶች መፍታት አይቻልም ብለው ያምናሉ”ም ብለዋል፡፡
የአሜሪካ አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ የታይዋን ጉብኝት ተከተሎ፤ በአሜሪካ ድርጊት የተበሳጨችው ቻይና ከአሜሪካ ጋር ያለትን ግንኙነት የማቋረጥ አዝማምያዎች እያሳየች ትገኛለች፡፡
በዚህም ቻይና ከአሜሪካ ጋር ወታደራዊ ትብብሮችን ማቋረጧን ያሳወቀች ሲሆን ተጨማሪ ውሳኔዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ሮይተርስ ዘግቧል።
ቻይና እስካሁን ከከፍተኛ ወታደራዊ ትብብሮች ባለፈ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ከዚህ በፊት የነበራትን የከፍተኛ መሪዎች የጋራ ውይይት መድረኮችን ከአሜሪካ ጋር ላለማድረግ መወሰኗን በውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ በኩል አሳውቃለች።
እንዲሁም ቻይና ከአሜሪካ ጋር የነበራትን የድንበር አልባ ወንጀል መከላከል፣ ስደተኞችን ማጓጓዝ፣ አደገኛ እጽ ዝውውር መከላከል እና ሌሎች ስምንት የትብብር መስኮችን አቋርጣለች።
ቻይና ሰሞኑን ታይዋንን በጎበኙት የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ ላይ ማዕቀብ መጣሏ ይታወሳል፡፡
የቻይና ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል ቀባይ ጽ/ቤት፤ ሀገሪቱ በናንሲ ፔሎሲ እና በቤተሰቦቻቸው ላይ ማዕቀብ መጣሏን ሲጂቲኤን ዘግቧል።