ቻይና ማዕቀብ የጣለችው በፔሎሲ ቤተሰቦችም ላይ ነው
ቻይና ሰሞኑን ታይዋንን በጎበኙት የአሜሪካ ምክር ቤት አፈጉባዐየ ናንሲ ፔሎሲ ላይ ማዕቀብ መጣሏን አስታወቀች፡፡
የቻይና ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቃል ቀባይ ጽ/ቤት፤ ሀገሪቱ በናንሲ ፔሎሲ እና በቤተሰቦቻቸው ላይ ማዕቀብ መጣሏን ሲጂቲኤን ዘግቧል።
ናንሲ ፔሎሲ በእስያ ጉብኝታቸው ታይዋንን ጎብኝተው ነበር፡፡
በአፈጉባዔዋ ጉብኝት የተቆጣችው ቤጅንግ፤ የአንድ ቻይና ፖሊሲ መርህ አንደተጣሰ እና ለዚህም አጸፋዊ ምላሽ እንደምትሰጥ ስትዝት ቆይታለች፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታ የቻይና ተዋጊ ጀቶች የታይዋንን ሰማይ አቋርጠው ገብተዋል፡፡ በአንድ ቀን ብቻ 27 የቻይና የጦር አውሮፕላኖች በታይዋን ሰማይ መብረራቸውን ቻይናም ታይዋንም ሲገለጹ ነበር፡፡
ቻይናን፤ በታይዋን ዙሪያ ወታደራዊ ልምምድ እያደረገች ሲሆን የሚሳኤል ተኩስም ማድረጓን መግለጿ ይታወሳል፡፡ ቻይና፤ የአሜሪካ አፈጉባዔ ታይዋንን በመጎብኘታቸው ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እርምጃ ልትወስድ እንደምትችል አስጠንቅቃ የነበረ ሲሆን ዛሬም በፔሎሲና በቤተሰቦቻቸው ላይ ማዕቀብ መጣሏል አሳውቃለች፡፡
ናንሲ ፔሎሲ በበኩላቸው፤ ወደ ታይዋን ያቀኑት፤ የቀጣናውን ነባር ሁናቴ ለመቀየር በማሰብ እንዳልሆነ አስታውቀዋል፡፡ አፈጉባዔ ፔሎሲ፤ ቻይና ታይዋንን ከዓለም አቀፍ መድረኮች “አስገልላ ልታስቀራት አትችልም” ሲሉ ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና አውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ሀገራትና ተቋማት በአንድ ቻይናን ፖሊሲ እንደሚያምኑ አስታውቀዋል፡፡ የአንድ ቻይና ፖሊሲ፤ ታይዋን፤ በቻይና መንግስት ስር እንደሆነችና የቻይና ሉዓላዊ ግዛት አካል እንደሆነች የሚያረጋግጥ መርህ ነው፡፡