ምዕራባውያን የቻይናን የመከላከያ በጀት ጭማሪ በስጋት ቢመለከቱትም፥ ቤጂንግ “ለማንኛውም ሀገር ስጋት አይሆንም” ብላለች
ቻይና የ2023 ወታደራዊ በጅቷን ልታሳድግ መሆኑ ተገለጸ።
የቻይና ኮሙዩኒስት ፓርቲ አመታዊ ጉባኤውን በነገው እለት ሲጀምርም የጭማሪው መጠን ይፋ ይደረጋል ተብሏል።
የሀገሪቱ ፓርላማ ቃል አቀባይ ዋንግ ቻኦ፥ የሚደረገውን የበጀት ጭማሪ ይፋ ባያደርጉም ካለፈው አመት የ7 በመቶ እድገት ሊኖረው እንደሚችል አሶሼትድ ፕረስ አስነብቧል።
ቻይና የወታደራዊ በጀቷን በ2023ትም ብታሳድግም ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርቷ አንጻር የሚኖረው ድርሻ ከዚህ ቀደሙ ከፍ ያለ እንደማይሆን ዋንግ ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ የቻይና ወታደራዊ በጀት ጭማሪ ለየትኛውም ሀገር ስጋት እንደማይሆንም ገልጸዋል።
ጭማሪው “ከሚታሰበው በተቃራኒ የቀጠናውን ብሎም የአለም ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ ያግዛል” ነው ያሉት ዋንግ ቻኦ።
የቻይናን ታላቅ ሀገርነት ታሳቢ አድርጓል የተባለው የወታደራዊ በጀት ጭማሪ ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነጻጸር አሁንም ዝቅተኛ መሆኑን በመጥቀስም ከምዕራባውያን የሚነሳውን ስጋት አጣጥለውታል።
ቻይና በ2021 ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርቷ (ጂ ዲ ፒ) 1 ነጥብ 7 ከመቶውን ነው ለወታደራዊ በጀት የምትይዘው።
በአንጻሩ በርካታ የውጭ ሀገራት ወታደራዊ ተልዕኮዎች ያሏት አሜሪካ ከጠቅላላ ምርቷ 3 ነጥብ 5 ከመቶው ለመከላከያ እንደምትበጅት የአለም ባንክ መረጃ ያሳያል።
ከ 2 ሚሊየን በላይ ወታደሮች ያሏት ቤጂንግ ባለፈው አመት ለመከላከያ ሃይሏ የያዘችው የ229 ቢሊየን ዶላር በጀት ከ2013 በእጥፍ ያደገ ነው።
የአለማችን ግዙፉን ባህር ሃይል የገነባችውና ሶስተኛውን ጠንካራ አየርሃይል እውን ያደረገችው ቤጂንግ ለወታደራዊ ሃይሏ በየአመቱ የምታወጣው ወጪ በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን ምዕራባውያን በስጋት ይመለከቱታል።
በጂቡቲ ወታደራዊ ጣቢያ መገንባቷ እና በደቡባዊ ቻይና ባህር ተጽዕኖዋን የሚያጎሉ እንቅስቃሴዎችን እያደረገች የምትገኘው ቻይና በታይዋን ላይ “ወረራ” ልትፈጽም ዝግጅቷን አጠናቃለች በሚልም ይከሷታል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ቤጂንግ ከዩክሬን ጋር ጦርነት ውስጥ ላለችው ሞስኮ የጦር መሳሪያ ልታቀርብ ትችላለች የሚለው ወቀሳና ዛቻ ጎላ ብሎ እየተደመጠ ነው።
እስያዊቷ ሀገር ግን የሃያላኑ ጦርነት በንግግር ይፈታ ዘንድ ባለ12 ነጥብ የሰላም እቅድ ይፋ በማድረግ ለሰላም ቅድሚያ እንደምትሰጥ መግለጿ ይታወሳል።