አሜሪካ ከቻይና ጋር ሊኖራት ስለሚችለው ጦርነት እቅድ መንደፏ ተገለጸ
አሜሪካ ከቻይና ጋር ወደ ጦርነት መግባቷ እርግጥ ወደ መሆኑ መቃረቡን አስታውቃለች
ዋሽንግተን በእስያ ሀገራት የየብስ ላይ ጦርነት ማድረግ አያዋጣኝም ብላለች
አሜሪካ ከቻይና ጋር ሊኖራት ስለሚችለው ጦርነት እቅድ መንደፏ ተገለጸ።
የዓለማችን ቀድሚ እና ተከታይ ልዕለ ሀያል ሀገራት የሆኑት አሜሪካ እና ቻይና ግንኙነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተካረረ መጥቷል።
ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ወደ ጦርነት ማምራቷን ተከትሎ አሜሪካ እና ሌሎች የምዕራባዊያን ሀገራት በሩሲያ ላይ ማዕቀብ ጥለዋል።
ሩሲያን ከተቀረው ዓለም ለመነጠል በሚል በምዕራባዊያን ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንደ ቻይና ባሉ ሀገራት ምክንያት ውጤታማ እንዳልሆነ ተገልጿል።
በዚህም ምክንያት አሜሪካ ከቻይና ጋር መካረር ውስጥ የገባች ሲሆን ታይዋንን ምክንያት በማድረግ ወደ ጦርነት ሊገቡ እንደሚችሉ ተገልጿል።
ቪኦኤ ዛሬ ይዞት በወጣው ዘገባ መሰረት አሜሪካ ከቻይና ጋር ሊኖራት ስለሚችለው ጦርነት እቅድ በማውጣት ላይ ትገኛለች።
የአሜሪካ መከላከያ ሚንስትር ዋና ጸሀፊ ክሪስቲን ዋርሙዝ እንዳሉት አሜሪካ ከቻይና ጋር የሚኖራትን ጦርነት ማሸነፍ የሚያስችል እቅድ እያወጣች ነው ብለዋል።
ከእቅዶቹ መካከልም በእስያ ተጨማሪ ወታደሮችን ማስፈር፣ ሀይፐር ሶኒክ ሚሳኤል የታጠቁ የባህር ሀይል ማስፈር፣ እና የየብስ ላይ ጦርነት እንዳይኖር ማድረግ፣ የበይነ መረብ ጦርነት እና ሌሎችም ይገኙበታል።
ከዚህ በተጨማሪም አሜሪካ ከቻይና ጋር ለሚኖራት ጦርነት አውስትራሊያ ፣ ጃፓን፣ ፊሊፒንስ እና ሲንጋፖር ጋር እንደምትተባበርም ተገልጿል።
እንዲሁም አሜሪካ በቀጣዮቹ ስምንት ወራት ውስጥ በህንድ-ፓስፊክ ውቂያኖስ አካባቢ ጠንካራ የምድር፣ ባህር እና የአየር ሀይል ወታደራዊ ማዘዣ ማቋቋም እንደምትፈልግም አስታውቃለች።
ይህ ወታደራዊ ማዘዣም በአካባቢው ላሉ ወዳጅ ሀገራትን ከጥቃት መጠበቅ ዋነኛው ስራው ይሆናል የተባለ ሲሆን ከቻይና ጥቃት ከተሰነዘረ ደግሞ በቀጥታ ወደ ጦርነት ይገባልም ተብሏል።