23 ዶላር ዘርፎ ከፖሊስ ለመሰወር 14 አመታትን በጫካ የተደበቀው ቻይናዊ ተያዘ
ግለሰቡ ከፖሊስ ለማምለጥ ያደረገው ሙከራ አብዝቶ ቢቀጣውም የሶስት አመታት እስር ይጠብቀዋል ተብሏል
ቻይናዊው ከፖሊስ እይታ ለመሰወር ባደረገው ጥረት በአባቱ ቀብር ላይ አልተገኘም፤ የልጁ ሰርግም አልፎታል
በፈረንጆቹ 2009 በቻይናዋ ሁቤይ ግዛት ኢንሺ ከተማ የተፈጸመው የዘረፋ ወንጀል ሊኦ ማውፉን ለ14 አመታት ሰላም ነስቶታል።
በወቅቱ እድሜው በ30ዎቹ አጋማሽ ይገኝ የነበረው ማውፉ ከእህቱ ባልና ሌሎች ጓደኞቹ ጋር በመሆን በከተማዋ የሚገኝ ነዳጅ ማደያን ሰብረው በመግባት 156 የቻይና ዩዋን ወይም 22 ነጥብ 5 የአሜሪካ ዶላር ይዘርፋሉ።
ከዘረፉት ላይም 60 ዩዋን ወጪ አድርገው ምግብና መጠጥ ሲሸምቱ ለእያንዳንዳቸው የሚከፋፈሉት ገንዘብ 32 ዩዋን ወይም 4 ነጥብ 6 ዶላር ይደርሳል።
ሶስቱ የሊዮ የዝርፊያ ግብረ አበሮች ከቀናት በኋላ መያዛቸውም የያኔውን ወጣት አስደንግጦታል፤ ፖሊሶች ቤቱ ደርሰው ይዘውት ወደ ማረሚያ ቤት ከሚወስዱትም ማምለጥን መረጠ።
ሊዮ እስርን ያመለጠ ቢመስለውም ለ14 አመታት በጫካ ውስጥ ተደብቆ ራሱን በእስራት ቀጥቷል።
ግለሰቡ ከመኖሪያ ቤቱ 10 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ጫካ ውስጥ ዋሻ ቆፍሮ ተደብቆ መኖር እንደጀመረ ርሃቡ ሲጠናበት ወጣ እያለ ቲማቲምና ሌሎች ፍራፍሬዎችን መስረቅ ይጀምራል።
በጫካ ውስጥ ያስደበቀው ስርቆት ድጋሚ ሰዎች እጅ ላይ እንዳይጥለው በመስጋትም እንሰሳትን እያደነ መብላት ይመርጣል።
ሊዮ ማውፉ የሚስቱ እና ልጆቹን ናፍቆት አልችል ሲልም ሰዎች በአደባባይ በዓላትን በሚያከብሩበት ጊዜና በምሽት ተደብቆ ይሄድና ጠይቋቸው ይመለሳል።
ቤተሰቦቹ ያለበትን ስፍራ እንዲያሳውቃቸው ቢወተውቱትም አሻፈረኝ በማለቱ ለጥቂት አመት በእስራት ሊያስቀጣ የሚችል እስራትን የሸሸው ሊዮ 14 አመታትን ራሱን በራሱ ለማሰር ተገዷል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ ብቸኝነቱ እና የቤተሰብ ናፍቆቱ እያየለበት ሲሄድ ግን በዚህ አመት እጁን ለፖሊስ ሰጥቷል ይላል የኦዲቲ ሴንትራል ዘገባ።
በወጣትነት እድሜው እስራትን ሽሽት ዱር ቤቴ ያለው ሊዮ አሁን የ50 አመት ጎልማሳ ሆኖ ሰውነቱም ገርጅፎ ወደፈራው እስር ቤት ተወስዷል።
ሊዮ ማውፍ ራሱን በጫካ ውስጥ በደበቀበት ወቅት የአባቱን መቅበርም ሆነ ወንድ ልጁን መዳር አልቻለም። ልጁ ባለፈው ወር የመጀመሪያ ልጁን ሲያገኝም ከአጠገቡ አልነበረም።
“አሁን እድሜዬ ከ50 አልፏል፤ የሚስቴም የጤና ሁኔታ ጥሩ አይደለም፤ የልጅ ልጅም አግኝቻለሁ” ያለው ሊዮ በመጨረሻም “የተረጋጋ ህይወት መኖር እፈልጋለሁ” ብሎ ራሱን ካሰረበት ወጥመድ ፈቷል።
የፖሊስ ሽሽቱ አብዝቶ ቢቀጣውም እስከ ሶስት አመት የሚደርስ እስር ግን አይቀርለትም ተብሏል።