የአሜሪካና ጀርመን መሪዎች በዋይትሃውስ ሩሲያ እና ቻይናን ስለመቅጣት መከሩ
የጀርመኑ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሹልዝ እና ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ባደረጉት ምክክር ለኬቭ 400 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ የጦር መሳሪያ ድጋፍ ይፋ ተደርጓል
ባይደን እና ሹልዝ ቻይና ለሩሲያ የጦር መሳሪያዎችን የምታቀርብ ከሆነ ሊጣልባት ስለሚችለው ማዕቀብም ተወያይተዋል
አሜሪካ እና ጀርመን ከዩክሬን ጋር ጦርነት ውስጥ ባለችው ሩሲያ ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ ለመውሰድ መስማማታቸው ተነግሯል።
የጀርመኑ መራሄ መንግስት ኦላፍ ሹልዝ ትናንት በዋይትሃውስ ከፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር ሲወያዩ ነው በሞስኮ ላይ የተባበረ ክንዳቸውን ለማሳረፍ የዛቱት።
ባይደን እና ሹልዝ ለአንድ ስአት የቆየ ምክክራቸው ሙሉ ትኩረቱን በዩክሬንና ሩሲያ ጦርነት ላይ አድርጓል ተብሏል።
ፕሬዝዳንት ባይደን በዚሁ ወቅት በርሊን ለኬቭ “ሊፓርድስ 2” ታንኮቿን ለመስጠት መስማማቷን አድንቀዋል።
ጀርመን ታንኮቹን ማቅረብ በጦርነቱ ውስጥ እጇን በቀጥታ እንደማስገባት ሊቆጠር ይችላል በሚል እምቢታዋን ስትገልጽ ብትቆይም የምዕራባውያኑን ጫና መቋቋም አልቻለችም።
ዩክሬን፥ የአውደ ውጊያ ማርሽ ቀያሪ ናቸው የሚባልላቸውን ጀርመን ሰራሽ ሊዮፓርድስ 2 ታንኮች በርሊንም ሆነች የሸጠችላቸው የአውሮፓ ሀገራት በፍጥነት እንዲያቀርቡላት እየወተወተች ነው።
ሩሲያ እነዚህን ታንኮች ማውደምና መማረክ መጀመሯን በገለጸች ማግስት ዋይትሃውስ የዘለቁት ኦላፍ ሹልዝ፥ “የትኛውንም የሚጠይቀውን ዋጋ ከፍለን ለዩክሬን መድረስ ይገባናል” ሲሉ ተደምጠዋል።
ባይደን እና ሹልዝ በነጩ ቤተመንግስት ምክክራቸው በሩሲያ ላይ ሊወሰዱ የሚችሉ እርምጃዎችን ከመዳሰሳቸው ባሻገር ቻይናም የውይይታቸው ርዕሰ ጉዳይ ነበረች ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
ቤጂንግ ለሞስኮ የጦር መሳሪያዎችን ልታቀርብ ትችላለች የሚለውን መረጃ ደጋግማ እየገለጸች ያለችው አሜሪካ ሊጣሉ የሚችሉ ማዕቀቦችን በተመለከተ ከአጋሮቿ ጋር እየመከረች መሆኑ ተገልጿል።
ከቻይናም ሆነ ከሩሲያ ጋር የጠበቀ የንግድ ግንኙነት የነበራት ጀርመን አቋሟን ይበልጥ ከምዕራባውያኑ ጋር እያስተካከለች ሄዳለች።
ቤጂንግን ለሞስኮ የጦር መሳሪያ እንዳትሰጥ ከማሳሰብ ጀምሮ ሩሲያ ላይ ተንጠልጥሎ የነበረውን የነዳጅ ፍላጎቷን ለማሟላት ሌሎች ሀገራትን ማማተር መያዟ ለዚህ ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።
መራሄ መንግስት ኦላፍ ሹልዝም ከታህሳስ 2021 ወዲህ ወደ ዋሽንግተን በማቅናት ያደረጉት ምክክር የበርሊን እና ሞስኮን ፍጥጫ እንዳያንረው ተሰግቷል።
በመሪዎቹ ምክክር ለዩክሬን 400 ሚሊየን ዶላር የሚያወጡ የጦር መሳሪያዎች ድጋፍ ለማድረግ ቃል ተገብቷል።
አሜሪካ ብቻ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ከ28 ቢሊየን ዶላር በላይ የሚገመት ድጋፍን ለኬቭ አድርጋለች።