ተማሪዎቹ ከ42 ሺ በሚልቁ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ይማሩ የነበሩ ናቸው
ኮሮና በኢትዮጵያ ከ26 ሚሊዬን በላይ ተማሪዎችን ከትምህርት ገበታ ውጭ አድርጓል
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ መከሰቱን ተከትሎ ከ42 ሺ በላይ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ይማሩ የነበሩ ከ26 ሚሊዬን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ ናቸው ተባለ፡፡
ተማሪዎቹ በአዲሱ ዓመት ወደ ትምህርት ገበታቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ በተመለከተ የትምህርት ሚኒስቴር መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የ2013 ዓ/ም ትምህርትን ለመጀመር የሚስችሉ ሁኔታዎችን ለመቃኘት የጥናት ቡድን ተቋቁሞ እየሰራ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ ትምህርት ቤቶች በአንድ ክፍል ውስጥ ከ20-25 ተማሪዎችን ማስተማር ይችሉ አይችሉ እንደሆነ ልየታ እየተካሄድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ርቀትን ለማስጠበቅ በአንድ ወንበር አንድ ተማሪ እንዲቀመጥ የሚደረግ ሲሆን ትምህርት በፈረቃ እንደሚሰጥም ገልጸዋል፡፡
ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች ይገነባሉ የማህበረሰብ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትም ለማስተማሪያነት ይውላሉ የሚል አማራጭም ቀርቧል፡፡
ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ ሁሉም ክልሎች በየትምህርት ቤቱ ተጨማሪ ክፍሎችን እንዲገነቡ እየተደረገ እንደሚገኝምና አስቀድመው የገነቡ አንዳንድ ክልሎች እንዳሉም ነው ሚኒስትር ዴዔታው የተናገሩት፡፡
ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስችሉ ግብዓቶችን በትምህርት ቤቶች ውስጥ የማቅረብ ስራዎች ይሰራሉም ብለዋል፡፡