የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን በመክፈት እንደሚጀመር ተገልጿል
የዘንድሮው ትምህርት መቼ ይጀመራል?
በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የቆየውን መደበኛ የትምህርት ስርዓት ለማስጀመር አስፈላጊውን ሁሉ ዝግጅት በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ስርዓቱ በወረርሽኙ ምክንያት ላለፉት 7 ወራት ተቋርጦ መቆየቱን ያስታወቀው ሚኒስቴሩ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል፣ የውሃ እና የእጅ ማፅጃ አቅርቦቶችን በማሟላት እና ትምህርት ቤቶችን የማፅዳት ስራዎችን በማከናወን መደበኛ ትምህርት እንደሚጀመር ገልጿል፡፡
ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ዶ/ር ኢንጂ.) ትምህርት በአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች የሚጀመር መሆኑን እና በቀጣይም ሌሎች የትምህርት ክፍሎች ወደ መደበኛ ትምህርት ስርዓቱ እንደሚገቡ ተናግረዋል፡፡
ወረርሽኙን ለመከላከል የተቀመጡ ጥንቃቄዎች ሙሉ በሙሉ ይተገበራሉ ያሉ ሲሆን ትምህርት በፈረቃ እንደሚሰጥም አብራርተዋል፡፡
የፈረቃ ስርዓቱ እንደየአካባቢው ሁኔታ ከ 2 እስከ 3 ሊሆን ይችላልም ነው ሚኒስትሩ ያሉት፡፡
በትምህርት ቤት ውስጥ መምህራኖች ትልቁን ሃላፊነት ሊወጡ ይገባል የተባለም ሲሆን ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ሲልኩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ ቀርቧል።
ሆኖም መደበኛ ትምህርቱ መንግስት ውሳኔ እንዳሳለፈ የሚጀመር ነው ከሚኒስቴሩ ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ እንደተገኘው መረጃ፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስፈላጊውን የጥንቃቄ እርምጃዎችን በመተግበር ትምህርት ቤቶችን መክፈት እንደሚቻል ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ምክረ ሃሳብ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡
ሚኒስቴሩ ያቀረበውን መነሻ በማድረግም በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች፣ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳዮች እና የህግ፣ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡
ትምህርት ከመጀመሩ በፊት የቅድመ ጥንቃቄ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መሰራት እንዳለባቸውም ነው በውይይቱ የተነሳው፡፡
በዩኒቨርስቲዎችና በቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ማዕከላት ላይ እንዴት ሊጀመር እንደሚችልና ምን ምቹ ሁኔታዎች እንዳሉም ቋሚ ኮሚቴዎቹ መክረዋል፡፡
በወረርሽኙ ምክንያት ከ26 ሚሊዬን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ ኮቪድ 19 ከሰዎች ጋር ሊቆይ የሚችል በመሆኑ ትምህርትን ለማስጀመር የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ላይ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የመማር ማስተማሩን ሂደት ጤናማ ለማድረግ በወጣው መመሪያ አዲስ ስታንዳርድ ወጥቶ ከዚህ በፊት እስከ 60 ተማሪዎችን የሚይዘው የመማሪያ ክፍል ከ20-25 ተማሪዎችን ብቻ እንዲይዝ መደረጉንና አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ለማሟላት ከአቅራቢ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር ) በበኩላቸው በመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለማስቀጠል የሚያስችል የቁሳቁስ ችግር በመኖሩ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የተቋረጠ ቢሆንም ሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች የገጽ ለገጽ ትምህርት ባለማስፈለጉ በተለያዩ ዘዴዎች ትምህርቱ ሲሰጥ መቆየቱንና አብዛኛዎቹ እየተመረቁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በቀጣይ ለተመራቂ ተማሪዎች ቅድሚያ እንደሚሰጥም ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያነሱት፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱን መልሶ ለመክፈት የሚያስችል ውይይት በጅማ ዩኒቨርስቲ አዘጋጅነት በመካሄድ ላይ ነው፡፡