የመስቀል ደመራ በዓል ከ 5 ሺህ ያልበለጡ ምዕመናን ብቻ በተገኙበት እንደሚከበር ተገለጸ
ከኮቪድ-19 በተጨማሪ የመስቀል አደባባይ ወቅታዊ የማስተናገድ አቅምም ምክንያት ነው ተብሏል
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በኮቪድ-19 ምክንያት በዓሉ በቀድሞ ድምቀቱ አይከበርም ብላለች
የመስቀል ደመራ በዓል የተወሰኑ ምዕመናን ብቻ በተገኙበት እንደሚከበር ተገለጸ
የዘንድሮው የመስቀል ደመራ በዓል የኮቪድ-19 ወረርሽን ለመከላከል ሲባል የተወሰኑ ምዕመናን በተገኙበት እንደሚከበር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አስታወቀች።
የዘንድሮው የደመራ በዓል ስርዓቱ እንደተጠበቀ ሆኖ በኮቪድ-19 ምክንያት አነስተኛ ምዕመናን በተገኙበት እንደሚከበር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የፓትርያርኩ ልዩ ጽህፈት ቤትና የውጭ ጉዳይ የበላይ ኃላፊ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ (ዶ/ር) መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በዩኔስኮ ቅርስነት የተመዘገበው የመስቀል ደመራ በዓል ቤተክርስቲያኗ ከምታከብራቸው የአደባባይ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላት መካከል አንዱ ነው።
የመስቀል ደመራ በየዓመቱ በደማቅ ሃይማኖታዊ ሥነ ስርአት ብዙ ህዝብ ተገኝቶ የሚያከብረው ደማቅ በዓል መሆኑ ይታወቃል፡፡
ይሁንና አንድ ሳምንት በቀረው በቀጣዩ የ2013 የደመራ በዓል በአጠቃላይ እስከ 5 ሺህ ተሳታፊዎች በመስቀል አደባባይ ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ብፁዕ አቡነ አረጋዊ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ አረጋዊ (ዶ/ር)
በዘንድሮ በዓል የተሳታፊ ሰዎች ቁጥር የተወሰነው ካለው ወቅታዊ የወረርሽኙ ሁኔታ በተጨማሪ መስቀል አደባባይ በአሁኑ ወቅት ማስተናገድ የሚችለውን መጠን ግምት ውስጥ በማስገባት መሆኑንም ያነሱት ብፁዕነታቸው ይህንንም የጠቅላይ ቤተክህነት ለሚመለከተው አካል ማሳወቁን ነው የገለጹት።
የመስቀል አደባባይ ለበዓሉ ዕለት ክፍት እንደሚሆንና ለዚህም አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መግለጹንና ይሄንንም አስተዳደሩ በአካል ተገኝቶ መመልከቱን አስረድተዋል።
ምንም እንኳን 5 ሺ ያህል ምዕመናን ብቻ እንደሚሳተፉ ቢገለጽም የሚመረጡት ምዕመናኑ በምን መንገድ እንደሚመረጡ በዘገባው የተባለ ነገር የለም፡፡