ለአንድ ወር ገደማ ተሰውረው የሰነበቱት ኪን ጋንግ በመጨረሻም ከስልጣን መነሳታቸው ተሰምቷል
ቻይና የቀድሞውን ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዳግም ወደ ስልጣን መለሰች።
ፕሬዝዳንት ሺ ጂፒንግ ለሶስተኛ ጊዜ በስልጣናቸው እንዲቀጥሉ በተመረጡበት የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ጉባኤ መጠናቀቅን ተከትሎ ነበር ኪን ጋንግ አዲስ ሹመት ያገኙት።
የፕሬዝዳንቱ የቅርብ ሰው ናቸው የተባለላቸው ኪን ላለፉት 30 ቀናት ከእይታ ርቀው ተሰውረው ቆይተዋል።
የሚንስትሩ መሰወርን ተከትሎ በርካታ መላ ምቶች ይቀርቡ የነበረ ሲሆን የብዙዎችን ትኩረት ስቦ የነበረው ግን ከፕሬዝዳንት ሺ ፒንግ ጋር ሳይጋጩ አልቀሩም የሚለው ነበር።
በበርካታ የዓለም ሚዲያዎች ደፋሩ ዲፕሎማት የሚል ስያሜ ይሰጣቸው የነበሩት እኝህ ዲፕሎማት አሁን ላይ ከስልጣን መነሳታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
በቻይና ሚንስትር ታሪክ ወጣቱ ሚንስትር የሚባሉት ጋንግ ከሹመታቸው በኋላ በአፍሪካ፣ በአውሮፓ እና እስያ ሀገራት ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን በርካታ ሀገራትም ቤጂንግን እንዲጎበኙ ማድረጋቸው ተገልጿል።
የ57 ዓመቱ ኪን ጋንግ የቻይና ውጪ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ፣ በብሪታንያ እና ዋሽንግተን የቤጂንግ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል።
ሚንስትሩ በኢንዴኔዢያ በተካሄደው የእስያ ሀገራት መሪዎች ጉባኤ ላይ በጤና እክል ምክንያት እንደማይገኙ ከተናገሩ በኋላ በአደባባይ ሳይታዩ ሰንብተዋል።
ከሰባት ወር በፊት ከሀላፊነታቸው ተነስተው የነበሩት ዋንግ ዪ ዳግም የቻይና ውጪ ጉዳይ ሚንስትር ተደርገው ተሹመዋል።
አዲሱ ተሿሚ ከሰሞኑ ወደ አፍሪካ መጥተው ከኢትዮጵያ እና ሌሎች ሀገራት መሪዎች ጋር ተመካክረው መመለሳቸው ይታወሳል።