የሩሲያና ቻይና ከፍተኛ ባለስልጣናት በዚህ ሳምንት ሰሜን ኮሪያን ይጎበኛሉ
ከ1950 እስከ 1953 የተካሄደው የኮሪያ ጦርነት በተኩስ አቁም የተጠናቀቀበትን እለት ሰሜን ኮሪያ እንደ ድል በዓል ታከብረዋለች
በምዕራባውያን የተለያየ ማዕቀብ የተጣለባቸው ሀገራት ትብብራቸውን እያጠናከሩ ነው
ሁለተኛው የአለም ጦርነት ሲጠናቀቅ በጃፓን ቅኝ ግዛት የነበረችው ኮሪያ ለሁለት ተከፍላለች።
በሶቪየት ህብረት የምትደገፈው ሰሜን ኮሪያ በፈረንጆቹ ሰኔ 25 1950 በአሜሪካ የምትታገዘውን ደቡብ ኮሪያ በመውረሯም ደም አፋሳሽ ጦርነት ተካሂዷል።
ለሶስት አመት የዘለቀው ጦርነት ከ3 ሚሊየን በላይ ሰዎችን ህይወት ቀጥፎም ኮሪያን አንድ ሳያደርጋት ሃምሌ 27 1953 በተኩስ አቁም ስምምነት ጦርነቱ መቆሙን የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ።
ሰሜን ኮሪያ የተኩስ አቁም ስምምነት የተደረገበትን እለት የድል በዓሏ አድርጋ የምታከብረው ሲሆን፥ ዘንድሮም ከሁለት ቀናት በኋላ 70ኛ አመቱን ታከበራለች።
በዚህ በዓል ላይ ታዲያ የሰባት አስርት ወዳጇን ሩሲያ ጨምሮ የቻይና እና ሌሎች አጋር ሀገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት እንዲታደሙ ጋብዛለች።
ሩሲያ በመከላከያ ሚኒስትሯ ሰርጌ ሾጉ የሚመራ ልኡክ በበዓሉ ላይ እንዲታደም እንደምትልክ ማሳወቋን የሰሜን ኮሪያ ብሄራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።
የቻይና ኮሚዩኒስት ፓርቲም የሀገሪቱ ፓርላማ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑትን ሊ ሆንግዦንግ ወደ ፒዮንግያንግ እንደሚልክ ተገልጿል።
የሩሲያ እና ቻይና ባለስልጣናት ከሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጋር የሁለትዮሽ ትብብርን ማጠናከር የሚያስችሉ ምክክሮችን እንደሚያደርጉም ነው የሚጠበቀው።
የመንግስታቱ ድርጅት በፒዮንግያንግ የኒዩክሌር ፕሮግራም ዙሪያ ማዕቀብ ለመጣል የውሳኔ ሃሳብ ሲያቀርብ በተደጋጋሚ የተቃወሙት ቤጂንግ እና ሞስኮ ከተገለለችው ሀገር ጋር ጥብቅ ወዳጅነት አላቸው።
የሺ ጂንፒንግ አስተዳደር በተለይ በሰሜን ኮሪያ የአስተዳደር ለውጥ ቢደረግ የሚፈጠረው የስደተኞች ጎርፍ ያሳስባቸዋል ነው የሚባለው።
ሩሲያ በየካቲት ወር 2022 በዩክሬን ጦርነት ካወጀች ጀምሮ ለሞስኮ ድጋፏን የምትሰጠው ፒዮንግያንግ፥ የጦር መሳሪያ ጭምር እየላከች ነው የሚል ወቀሳ ከአሜሪካ ይቀርብባታል።
የምዕራባውያን ጫና እና ማዕቀብ ይበልጥ ያስተሳሰራቸው ሀገራት ታሪካዊ ግንኙነታቸውን ለማደስ የሀሙሱን የድል በዓል ሊጠቀሙበት ይችላሉም ተብሏል።
ከ2022 ወዲህ ከ100 በላይ ሚሳኤሎችን ያስወነጨፈችው ሰሜን ኮሪያ 70ኛ አመት የድል በዓሏን ስታከብር አዳዲስ እና ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎቿን እንደምታሳይ ይጠበቃል።