የቻይናው የኤሌክትሪክ መኪና አምራች ቢዋይድ የቴስላን የሽያጭ ደረጃ ለመንጠቅ መቃረቡ ተገለጸ
ኩባንያው በታህሳስ ወር ብቻ ከ207 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎችን የሸጠ ሲሆን በአጠቃላይ ባለፈው የፈረንጆቹ አመት 1.7 ሚሊየን ተሸከርካሪዎችን መሸጥ ችሏል
ቢዋይድ 90 በመቶ ምርቱን ለቻይና ገበያ የሚያቀርብ ቢሆንም በመላው አለም ያለው ተቀባይነት እያደገ ነው ተብሏል
የቻይናው የኤሌክትሪክ መኪና አምራች ቢዋይዲ በ2024 መጨረሻ ያስመዘገበው ሺያጭ በአለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የገበያ ተወዳዳሪነት እንዳጠናከረው ተገልጿል፡፡
ኩባንያው አጠቃላይ በአመቱ እና በአመቱ የመጨረሻ ሶስት ወራት በኤሌክትሪክ መኪና ሽያጭ ያስመዘገበው ውጤት የአሜሪካውን ቴስላ ኩባንያ የሽያጭ ደረጃ ለመንጠቅ እንዲቃረብ አስችሎታል፡፡
ቢዋይዲ በታህሳስ ወር 207,734 መኪኖችን በመሸጥ አመታዊ አጠቃላይ የሽያጭ ድምሩን ወደ 1.76 ሚሊዮን አድርሷል፡፡
ኩባንያው ለሀገር ውስጥ ገበያ በሚያቀርባቸው ምርቶች ድጎማ እና የዋጋ ቅናሾችን ማድረጉ ደንበኞችን ለመሳብ አግዞታል፡፡
በየአመቱ 41 በመቶ የገበያ እድገት እያስመዘገበ የሚገኝው የቻይናው መኪና አምራች በኤሌክትሪክ እና በነዳጅ ጉልበት የሚሰሩ (ሀይብሪድ) ተሽከርካሪዎቹ ተፈላጊነታቸው ከፍተኛ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት 90 በመቶ ምርቶቹን በቻይና ገበያ የሚያቀርብ ሲሆን በዚህም ቶዮታ እና ቮልስዋገንን የመሳሰሉ ግዙፍ የመኪና አምራቾች በቻይና ያላቸውን የገበያ ድርሻ በመንጠቅ በአንድኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
የቢዋይዲ ተፈላጊነት እና የገበያ ድርሻ እያደገ መምጣት ቀደም ሲል ሰፊ የገበያ ተቀባይነት ያላቸው ታዋቂ መኪና አምራቾች በገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመዝለቅ ፈታኝ እንዲሆንባቸው አድርጓል፡፡
ባለፈው ወር ሁለቱ የጃፓን የመኪና አምራች ኩባያዎች ሆንዳ እና ኒሳን ከቻይና የመኪና ኢንዱስትሪ የሚገጥማቸውን ውድድር ለመቋቋም ለመወሀድ ውይይት መጀመራቸው መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የቻይናው ቢዋይዲ እድገት ቀጥሏል ያለው የቢቢሲ የቢዝነስ ዘገባ በ2024 ሶስተኛ ሩብ አመት ኩባንያው ያገኘው ትርፍ ከቴስላ እንደሚበልጥ አስነብቧል፡፡
ከሀምሌ እስከመስከረም ባለው ጊዜ ቢዋይዲ 28.2 ቢሊየን ዶላር ትርፍ ያገኝ ሲሆን ከባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም በ24 በመቶ እድገት የታየበት ነው፤ በወቅቱ የኢለን መስኩ ቴስላ የሶስት ወራት ትርፍ 25.2 ቢሊየን ዶላር ነበር፡፡
ኩባንያው ከቻይና ገበያ ተሸግሮ በአለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ተቀባይነት ለማስፋት በሚያደርገው ጥረት የተለያዩ የታሪፍ ጭማሪዎች መሰናክል ሆነውበታል፡፡
በጥቅምት ወር የአውሮፓ ህብረት ከቻይና በሚገቡ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ላይ የ45 በመቶ የታሪፍ ጭማሪ አድርጓል፤ አሜሪካም የ100 በመቶ ታሪፍ አስቀምታጣለች፡፡
እነዚህ የታሪፍ ጭማሪዎች በአዲሱ የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደርም ይቀጥላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡