በአፍሪካ በ2025 ዴሞክራሲያዊ ስርአትን ማጠናከር ለኢኮኖሚያዊ እድገት ቁልፍ ነው ተባለ
የፖለቲካ መረጋጋትንና የኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥ የተሻለ አስተዳደር እና ነጻ ምርጫ እንዲደረግ ባለሙያዎች ጠይቀዋል
የአስተዳደራዊ እና የዴሞክራሲያዊ ጥያቄዎች ባለተፈቱበት ኢኮኖሚን ማሳለጥ እንደማይቻልም ተነግሯል
በአፍሪካ አህጉር ዴሞክራሲን ማጠናከር በ2025 የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ ወሳኝ መሆኑን ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡
ለአብነት በሞዛምቢክ ፍሪሊሞ ፓርቲ የ49 አመት አስተዳደሩን ለማስቀጠል ምርጫ አጨበርብሯል በሚል የተነሳው አመጽ በአዲሱ አመትም እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡
በአፍሪካ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ኢንስቲትዩት የኢኮኖሚ እና የህብረተሰብ ጥናት ተመራማሪ ሰርዋህ ፕሪምፔህ የዲሞክራሲያዊ ልምምዶች እጦት እና ግልጽ ካልሆኑ ምርጫዎች ጋር ተያይዘው የሚፈጠሩ ችግሮች አሁንም አሳሳቢ ጉዳይ ሆነው የሚቆዩ ናቸው ብለዋል።
ቱኒዚያ እና ሞሪታኒያ ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ርምጃ ጀምረዋል፤ ነገር ግን በሁለቱም ሀገራት የተካሄዱት ምርጫዎች በህገ-ወጥነት መታየታቸውን ተመራማሪው ይጠቁማሉ፡፡
በሀምሌ ወር በሞሪታኒያ የፕሬዚዳንት መሀመድ ኡልድ ጋዙዋኒ መመረጥን በመቃወም በፀጥታ ሀይሎች እና በተቃዋሚዎች መካከል በተነሳ ከባድ ግጭት ቢያንስ ሶስት ሰዎች ተገድለዋል።
በ2025 ሀገራት ተቋሞቻቸውን ካላጠናከሩ የምርጫቸውን ታማኝነት ፣ ጥራት፣ግልጸኝነት እንዲሁም የመድበለ ፓርቲ ስርዓቱን ማሻሻል ካልቻሉ መሰል ክስተቶች በ2025 እንደሚቀጥሉ የኢኮኖሚ እና የህብረተሰብ ጥናት ባለሙያው አሳስበዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በ2024 በተካሄዱ ምርጫዎች ከአውራ ፓርቲ ወደ መድበለ ፓርቲ መንግስት ሰላማዊ ሽግግር ያደረጉ ደቡብ አፍሪካ እና ቦትስዋናን የመሳሰሉ ሀገራት መኖራቸው ተስፋን የሚያጭር ስለመሆኑ ተገልጿል፡፡
የምስራቅ አፍሪካ በአህጉሪቱ ፈጣን እድገት ያለው ቀጠና ሲሆን አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት ዕድገቱም በ2024 ከነበረበት 4.9 በመቶ በ2025 ወደ 5.7 በመቶ እንደሚያድግ የአፍሪካ ልማት ባንክ መረጃ ያመላክታል፡፡
ነገር ግን ይህ ቀጠና በጦርነቶች እና በትጥቅ ግጭቶች በሚሊየን የሚቆጠሩ ተፈናቃይ ዜጎች መገኛም ነው፡፡
የሀገር ውስጥ መፈናቀል ክትትል ማዕከል (አይዲኤምሲ) ሪፖርት እንደሚያመለክተው እ.ኤ.አ. በ2024 መጨረሻ 35 ሚሊየን አፍሪካውያን በትውልድ ሀገራቸው ተፈናቃይ ወይም ስደተኛ ሆነው ይኖራሉ፡፡
በአፍሪካ ውስጥ ከተፈናቀሉ ዜጎች 80 በመቶዎቹ በሱዳን፣ በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፣ ኢትዮጵያ፣ ናይጄሪያ እና ሶማሊያ ውስጥ ይገኛሉ፡፡
በሳህል ቀጠና ከአምስት ባላነሱ ሀገራት በተከታታይ የታየው መፈንቅለ መንግስት በቀደመው ስርአት የነበሩ ችግሮችን ከመቅረፍ ይልቅ እያወሳሰበ መቀጠሉን ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ፡፡
እነዚህ ሁሉ ከፖለቲካ አለመረጋጋት እና ከዴሞክራሲ እድገት መቀጨጭ ጋር የተያያዙ ችግሮች በዘለቁበት በአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ እድገትን ማሳለጥ አስቸጋሪ እንደሚሆን ዶቼቬለ አስነብቧል፡፡