“ሁሉም ሰው የየራሱ የህይወት መጽሀፍ ደራሲ ነው”- ሰዐሊ ብሩክ የሺጥላ
በታዳጊነቱ ያጋጠመው ያልተለመደ ህመም ከቡረቃው አስቁሞ በቤት አዋለው ብሩክ ተስፋ አልቆረጠም ነበር
ያለሰው እገዛ ሙሉ ሙሉ በሙሉ የመንቀሳቀስ የሚያስችለውን የጉልበት ንቅለ ተከላ በቅርቡ በስዊድን ለማድረግ እየተዘጋጀ ይገኛል
ሰዐሊ ብሩክ የሺጥላ ዛሬ ለሚገኝበት መንፈሰ ብርቱነት እና ጥንካሬ ደረጃ ላይ ለመድረስ ሁኔታዎች ሁሌም ቀላል እንዳልነበሩ ይገልጻል፡፡
ከ12 አመቱ ጀምሮ ነበር ሰውነቱን በነጻነት እንዳይንቀሳቀስ የሚያደደርግ ህመም ያጋጠመው። ነገር ግን እንደሌሎች በነጻነት አለመንቀሳቀሱ ከህልሙ እንዲያስቆመው አልፈቀደም፤ በዙዎች በደረቱ ተኝቶ በሚስላቸው የተለያዩ አይነት ስእሎች ያውቁታል፡፡
ይህ በአለም ላይ በጥቂት ሰዎች ላይ ብቻ የሚከሰተው በሽታ የመገጣጠሚያ አካላትን ፈሳሽ በማድረቅ የሰውነት ክፍል እንቅስቃሴን የሚገድብ ነው፡፡
ብሩክ በቅርቡ ወደ ስዊድን ሀገር በመሄድ የጉልበት ንቅለ ተከላ ለማድረግ በመዘጋጀት ላይ ይገኛል፡፡
ይህ ህክምና የሚሳካ ከሆነም አሁን ከሚገኝበት ሁኔታ በተሻለ ያለ ሰው እርዳታ እንዲንቀሳቀስ የሚያስችለው ነው፡፡
አል ዐይን አማረኛ በመኖሪያ ቤቱ ተገኝቶ አዲስ ስለሚያደርገው ህክምና ፣ ስለ ህይወት ልምዱ ፣ አሁን ስለሚገኝበት እና ስለ ስዕል ስራዎቹ ከሰአሊ ብሩክ የሺጥላ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- ብዙዎች የጽናት ምሳሌ ሲሉ ይገልጹሀል፤ ይህን ብርታት ከየት አገኝኸው?
ብሩክ፡- እኔ ያሳለፍኳቸው ችግሮች እና ፈተናዎች አሁን ለምገኝበት ብርታት ምንጮቼ ናቸው ብየ አስባለሁ፡፡
ሰው ትክክለኛ ማንነቱን የሚሰራው ወይም የሚቀርጸው በሚያልፋቸው ፈተናዎች ውስጥ እንደሆነ አምናለሁ፤ እኔም የችግሮቼ እና ፈተናዎቼ ውጤት ነኝ፡፡
ይህ በሽታ ሲከሰት እና አልጋ ላይ ሲያውለኝ ራስን ያለመቀበል ፣ ተስፋ መቁረጥ ፣ ራስን በመጥላት እና በሌሎች መጥፎ ስሜቶች ውስጥ ቢያንስ ለ9 እና ለ10 አመታት ኖሬያለሁ በእጄ ላይ ስላለው ነገር ሳይሆን ስለ እምሞትበት ቀን አጥበቄ ያሰላሰልኩባቸውን ጊዜያቶች አሳልፊያለሁ፡፡
ቀስ በቀስ ከሁኔታዎች ጋር ለመታረቅ ፣ ነገሮችን ለመቀበል እና አሁን ባለሁበት ሁኔታ ምን ማበረከት እንዳለብኝ ማሰብ ጀመርኩ፤ ከዛም ወደ ሀይማኖት ወደ ቤተክርስቲያን ይበልጥ ቀረብኩ መጽሀፍትን ወዳጆቼ አደረኩ ቀጥሎም ራሴን ከሌሎች ሰዎች ጋር ሳይሆን ከራሴ ጋር ማወዳደር ፣ መስራት ስለምችለው ነገር ብቻ ማሰብ ጀመርኩ። ከዚህ ጊዜ በኋላ ነው እንግዲህ ይበልጥ ስዕል ስራዎቼ ላይ ማተኮር የጀመርኩት፤ በእነርሱም ነው ሰዎች ጋር መድረስ የቻልኩት፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- ብዙዎች በትንሽ የህይወት ፈተና በብዙ ተስፋ ሲቆርጡ ይታያሉ አንተ ወደ ፊት እንድትገፋ ወደ ኋላ እንዳትመለስ ያደረገህ ነገር ምንድን ነው?
ብሩክ፡- እንደምታየው ከእጄ በስተቀር ሌላው የሰውነት ክፍሌ አይንቀሳቀስም። ነገሮች ሁሌም ምቹ ላይሆኑ ይችላሉ ፤ ነገር ግን እኔ ይህን አላስብም፤ ከዚህ ይልቅ ነገ ምን አዲስ ነገር መስራት እችላለሁ በህይወቴስ ውስጥ ምን ለውጥ ማምጣት እችላለሁ የሚለው ጥያቄ ላይ ብዙ ጊዜ አጠፋለሁ፡፡ ዛሬ ላይ በምሰራው ነገር ነገን እንድናፍቅ እና ለነገ እንድጓጓ ያደረገኝ ነገርም ይሄው ነው፡፡
ተስፋ በመቁረጥ ውስጥ በነበርኩበት ጊዜ ራሴን ከመናቅ እና እንደማልችል ከማሰብ ውጪ ያተረፍኩት ነገር የለም፤ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ቢሆን ከመሞከር እና ከመጣር እንጂ ተስፋ ከመቁረጥ ምንም የሚገኝ ነገር አለመኖሩን በደንብ ተገንዝቢያለሁ፡፡
ሁላችንም ወደዚህ ምድር ያለምክንያት አልመጣንም ወይም ያለ ምክንያት አልተፈጠርንም ሲመስለኝ እርሱን ቁምነገር መረዳት በህይወት ውስጥ ትልቅ ለውጥ እንድታመጣ የሚያግዝህ ነገር ነው፡፡
በጥረት ውስጥ የምታሳልፈው ዛሬ የምትፈራውን ነገን እንድታነፍቀው ያደርጋል ተስፋ የሚቆርጥ ሰው ባለበት የቆመ ወይም ለችግሮቹ እጅ የሰጠ ሰው ነው ብየ አስባለሁ፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- እስኪ ስለ ጤናህ ሁኔታ እናውራ የህመሙ አይነት ምን ይባላል አሁን የምትገኝበት ሁኔታስ ምን ይመስላል?
ብሩክ፡- አንኪሎዚንግስፖናዳላይተዝ የተባለ በሽታ ተጠቂ ነኝ። ህመሙ የጀመረኝ የ12 አመት ታዳጊ እያለሁ ነ፤ በዋናነት አጥንቶች ውስጥ የሚገኙ ፈሳሾችን በማድረቅ አጥንቶችን በማጠባበቅ ለመንቀሳቀስ እንዳትችል የሚያደርግ በሽታ ነው፡፡
አንገቴ ፣ የጀርባ እና የእግር አጥንቶቼ በሙሉ መንቀሳቀስ አይችሉም ለ14 አመት ያህል በዚህ ሁኔታ ውስጥ ኖሬያለሁ። ከ14 አመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሂፕ (የዳሌ) ንቅለ ተከላ ህክምና ካደረኩ በኋላ ከአልጋ ላይ ተነስቼ በድጋፍ መንቀሳቀስ ችያለሁ አሁን ያለሁበት ሁኔታ ይህን ይመስላል፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- በቅርቡ በስዊድን ሀገር የጉልበት ንቅለ ተከላ ልታደርግ እንደሆነ ሰምተናል። ለህክምናው ወጪ በሸራተን አዲስ “ነጻነት” የተሰኘ የስዕል ጨረታ ፕሮግራም አዘጋጅተህም ነበር ሂደቱ ምን ሁኔታ ላይ ነው የሚገኘው?
ብሩክ፡- የስዕል ጨረታ ፕሮግራሙን ያደረኩት ስነጥበብ እራሷን በራሷ ታድናለች በሚል መነሻ ነው ገንዘብ መዋጮ ለማሰባሰብ እና ድጋፍ ለመጠየቅ ፍላጎቱ አልነበረኝም፡፡
በተለይ በስዕል ላይ ለሚገኙ ወጣቶች እና ህጻናት ጥበብን በመጠቀም ቢያንስ ራሴን ማዳን መቻሌ ትልቅ ብርታት ሊሆን እንደሚችል መልዕክት ለማስተላለፍም ተጠቅሜበታለሁ፡፡
ለጨረታ ፕሮግራሙ ነጻነት የሚል ስያሜ የሰጠሁት ከጉልበት ንቅለ ተከላ ህክምናው በኋላ በነጻነት በራሴ ተንቀሳቅሼ መስራት የምችልበትን ሁኔታ በማሰብ ነው፡፡
ብዙ ጊዜ ተወዳድሬ በማሸነፍ በውጭ ሀገራት የስእል ስራዎቼን የማቅረብ እድል ገጥሞኝ ነበር፤ ሆኖም ፕሮግራሞቹ አብሮኝ የሚያግዘኝን ሰው ወጪን መሸፈን የሚያስችል በጀት ስለማይኖራቸው እነኚህ እድሎች አምልጠውኛል፡፡
እናም ከህክምናው በኋላ ያለብኝን በድንብ ተንቀሳቅሶ የመስራት ገደብ ይቀርፋል ብየ በማሰብ ስያሜውን ከነጻነት ጋር አገናኝቼዋለሁ፡፡
ህክምናውን የማደርገው አንተም እንዳልከው በስዊድን ሀገር ነው ለዚህም 3 ሚሊየን ብር ገደማ ያስፈልጋል ይህን ወጪ ለመሸፈን ነው የስዕል ጨረታውን ያዘጋጀሁት እግዚያብሔር ረድቶኝ የሚያስፈልገኝን ገንዘብ ማግኝት ችያለሁ፡፡
አሁን ጨረታውን ካሸነፉ ሰዎች ገንዘቡን በማሰባሰብ ላይ ነኝ ከጨረታው ባለፈም 40 የሚደርሱ ስዕሎችንም ለሽያጭ አቅርበን ነበር ፈጣሪ ከፈቀደ በፈረንጆቹ አዲስ አመት ጃንዋሪ ላይ ቀዶ ጥገናውን ለማድረግ ዝግጅቴን እየጨረስኩ እገኛለሁ፡
ህክምናውን ጨርሼ ከመጣሁ በኋላ ፊዚዮቴራፒን ጨምሮ ሌሎች የህክምና ወጪዎች ሊኖሩ ይችላሉ እሱንም የኦንላይን የስዕል ጨረታ በማድረግ ለመሸፈን አቅጃለሁ፡፡
አል ዐይን አማርኛ፡- በርካታ የስዕል ስራዎች እንዳሉህ ይታወቃል የምትጠቀማቸው የስዕል ግብአቶችም ለየት ያሉ ናቸው፡፡ እስካሁን ምንያህል የስዕል ስራዎችን እና ኤግዚቢሽኖችን አዘጋጀህ? በብዛት በስራዎችህ ማስተላለፍ የምትፈልጋቸው መልዕክቶችስ ምንድን ናቸው?
ብሩክ፡- እውነት ለመናገር የስዕል ስራወቼን በቁጥር አላውቃቸውም። አሁን ላይ ግን ስራዎቹን ለማሰባሰብ እና ለመመዝገብ እንዲሁም በመጽሀፍ መልክ ለማዘጋጀት ሀሳቡ አለኝ፤ በኤግዚቢሽን ደረጃ በግል 15 በቡድን ደግሞ ከ26 በላይ ኤግዚቢሽኖችን አዘጋጅቻለሁ፡፡
መልዕክትን በተመለከተ በስራዎቼ ላይ የሀሳብ ገደብ እንዲኖርብኝ አልፈልግ፤ ከህይወቴ የተማርኩትም በታጠረ ወሰን ውስጥ መኖር መልካም እንዳልሆነ ነው፡፡
ለዛም ነው በስራዎቼ ላይ ከሸራው ላይ ከሚገናኝ ቀለም እና ብሩሽ በዘለለ የተለያዩ ቁሶችን የምጠቀመው ለምሳሌ የእንቁላል ቅርፊትን መጠቀም አዘወትራለሁ፤ ይህን የማደረግው በተለይ እንቁላል የሰውን ልጅ ከውልደቱ እስከሞቱ ያለውን ኡደት ያሳያል ብየ ስለማስብ ነው፡፡ ይቅርታ ፣ ተስፋ ፣ ጽናት እና ሌሎችም 6 መልዕኮት ላይ በማተኮር ነው ስዕሎቼን የማዘጋጀው፡፡
አል ዐይን ከአማርኛ፡- ከስዕል ወጪ በሚኖርህ ጊዜ ምን በማድረግ ታሳለፋለህ የምትዝናናው በምንድን ነው?
ብሩክ ፡- ሰው በጣም እወዳለሁ በጣም ብዙ ጓደኞችም አሉኝ ከእነርሱ ጋር ጊዜ ማሳለፍ ደስ ይለኛል ስለጥበብ ፤ ስለማህበራዊ ጉዳዮች እና የጋራ በሚያደርጉን ነገሮች እየተጨዋወትን እናሳልፋለን፤ ከዚህ በተረፈ መጽሀፍ አነባለሁ ፣ ሙዚቃምም እወዳለሁ የሚካኤል በላይነህ እና የዘሪቱ ከበደ አድናቂ ነኝ፡
አል ዐይን አማርኛ፡- በመጨረሻም ከዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ በኋላ ስለ ህይወት ምን አመለካከት አለህ ብየ ብጠይቅህ መልስህ ምንድን ነው?
ብሩክ፡- ድሮ እኔ እንደገሌ ካልኖሩክ ወይም ካልሆንኩ መኖሬ ምን ትርጉም አለው ብየ አስብ ነበር ይህ የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው፡፡
ብዙዎቻችን የሌሎች ሰዎች ስኬት ላይ እናተኩር እና ያለንን ነገር አዳፍነን እንቅበረዋለን ምን መስራት እንደምንችል እንኳን በቅጡ አንገነዘብም፡፡
ሁሉም ሰው የየራሱ መጽሀፍ ደራሲ ነው፤ አጨራረሱን እና የመጽሀፉን አካሄድ የሚወስነው እራሱ ደራሲው ነው እያንዳንዱ ገጽ ላይ ዋጋ ያለው ነገር ሰለማኖር ፣ ስለመገንባት ማሰብ አለብን፡፡ ህይወት የሂደት ውጤት ናት ነገ የማይገፋ ግንብ ለመገንባት ዛሬ ላይ አንድ የምታስቀምጠው ጡብ መሰረት መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡
መጀመሪያ ከነድክመትህ ራስህን መቀበል ስትጀምር ነው ችግሮችህን ስለመቀርፍ ፈተናዎችን ስለማለፍ አልፎ ተርፎም ለሌሎች ሰዎች መትረፍ የምትችለው፡፡
ሰዎች ስኬታማ መሆን ይፈልጋሉ ነገር ግን ወደ ስኬት የሚወስዳቸውን መንገድ አልጀመሩትም፤ ቁጭ ብለህ ለውጥ አይመጣም እኔ አሁን ባለሁበት የጤና ሁኔታ ውስጥ ስለህይወት ይህን ያሀል በጎ አስተሳሰብ ካለኝ ፣ መስራት መለወጥ ፣ በምድር ላይ ጥሩ ተጽዕኖ መፍጠር እንደምችል የሚሰማኝ ከሆነ ሙሉ ጤንነት ላለው ሰው ይሄ እንዴት ሊከብደው ይችላል?
አል ዐይን አማርኛ፡- ለነበረን ጊዜ ከልብ እናመሰግናለን ህክምናው ተሳክቶ ወደ ሀገር እንድትመለስ ምኞታችን ነው!
ብሩክ፡- አሜን እኔም ሀሳቤን እንገልጽ ለሰጣችሁኝ ጊዜ ከልብ አመሰግናለሁ!