ቻይና የሰራቻቸውን የመንገደኛ አውሮፕላኖች በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት ለገበያ ማቅረብ ልትጀምር ነው
አዲሱ የቻይና የመንገደኞች አውሮፕላን `C919` የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል
የቻይና ወደ ገበያው መግባት ለአሜሪካው ቦይንግና ለፈረንሳዩ ኤር ባስ አዲስ ፈተናን ይዞ ይመጣል ተብሏል
ቻይና በራሷ አቅም የሰራቸው የመንገደኞች አውሮፕላን በያዝነው የፈረንጆቹ 2022 በብዛት በመመረት ለገበያ መቅረብ እንደሚጀመር ተገለፀ።
መቀመጫውን ሻንጋይ ያደረገው የቻይና የንግድ አውሮፕላን ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ስራ አስኪያጅ እንደተናሩት፤ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአውሮፕላኖቹ ምርት ላይ አሳድሮት የነበረው ጫና በቀላሉ መስተካከሉን ጠቅሰዋል።
አሁን ላይ አውሮፕላኖቹ እየተመረቱ መሆኑን ጠቅሰው፤ በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት አውሮፕላኑ እንዲመረትላቸው ላዘዙ ተቋማት ርክክብ ማድረግ እንደሚጀመር አስታውቀዋል።
የአውሮፕላን ምርት እንዲስትሪው በቢሊየን ዶላሮች የሚንቀሳቀስ ሲሆን፤ የአሜሪካው ቦይንግ እና አፈረንሳዩ ኤር ባስ ይህንን ኢንደስትሪ በበላይነት እንደሚመሩት ይታወቃል።
`C919` የሚል ስያሜ የተሰጠው አዲሱ የቻይና አውሮፕላን ወደ ገበያ ሲቀላቀል ለእነዚህ ግዙፍ የአውሮፓላን አምራቾች አዲስ ተፎካካሪ ይሆናል ተብሏል።
በተለይም የቻይና `C919` የመንገደኞች አውሮፕላን ከቦይንጉ 737 ማክስ እና ከኤርባስ A320 ጋር የሚፎካከር መሆኑን ሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘግቧል።
`C919` አውሮፕላን ከ158 እስከ 168 መቀመጫውች ያሉት ሲሆን፤ እስክ 12 ሺህ 100 ሜትር ከፍተታ ድረስ መብረር የሚችል መሆኑም ነው የተገለፀው።
በሰዓት እስከ 900 ኪሎ ሜትር የሚበረው አውሮፕላኑ፤ በአንድ ጊዜ ከ4 ሺህ 75 እስከ 5 ሺህ 555 ኪሎ ሜትር መብረር የሚችል መሆኑም ተነግሯል።
ቻይና ኢስተርን አየር መንገድ አምስት `C919` የመንገደኞች አውሮፕላን ከቻይና የንግድ አውሮፕላን ኮርፖሬሽን ለመግዛት መፈራረሙ ታውቋል።