ያለማቋረጥ ከ80 ሰዓታት በላይ የምትበር ድሮን የሰሩት የቻይና ተማሪዎች አዲስ ክብረ ወሰን አስመዘገቡ
ፌንግ አርዩ 3-100 ድሮን 10 ሜትር የክንፍ ርዝማኔ ያላት ሲሆን፤ በጋዝ ሞተር አማካኝነት ነው የምትንቀሳቀሰው
ድሮኗን የሰሩት ተማሪዎቹ አማካኝ ዕድሜ ከ20 ዓመት በታች እንደሆነ ተገልጿል
ቻይናዊያን ተማሪዎች ለረጅም ሰዓት የምትበር ድሮን በመስራት አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን በእጃቸው ማስገባታው ተሰምቷል።
በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተሰራችው ድሮኗ ያለ እረፍት ለረጅም ሰዓት የበረረች ድሮን በመባል የዓለም ክብረ ወሰንን እንደሰበረች የቴክኖሊጂ እና ኢኖቬሽን ኢኒስቲትዩት ዢኑዋን ጠቅሶ ያወጣው መረጃ ያለክታል።
ድሮኗ በቤጂንግ የኤሮናቲክስ እና አስትሮናቲክስ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተሰራች ሲሆን፤ ፌንግ አርዩ 3-100 የሚል መጠሪያ እንዳላትም ተጠቅሷል።
ድሮኗ ያለ ማቋረጥ ለ80 ሰዓት ከ46 ደቂቃ ከ35 ሴኮንድ መብረር የቻለች ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም በቦይንግ ስር በሚተዳደረው ኦሪዮን በተሰኘ ተቋም በ80 ሰዓት፣ ከ2 ደቂቃ ከ52 ሴኮንድ ተይዞ የነበረውን ክብረ ወሰን ማሻሻል እንደቻለችም ተነግሯል።
በረራው የተከናወነው ባሳለፍነው ግንቦት ወር በቻይና ሄናን ግዛት ውስጥ ነበር፤ ሆኖም ክብረ ወሰኑ ሳለፍነው ሳምንት እሁድ ነው በዓለም አቀፉ የኤሮናቲክስ ፌደሬሽን እውቅና ተሰጥቶት የተመዘገበው።
በበረራው ወቅት ድሮኗ በ300 ሜትር ከፍታ ላይ ስትጓዝ የነበረች ሲሆን፤ በአየር ላይ እያለችም ምንም አይነት ተጨማሪ ነዳጅ እንዳይሞላላት ተከልክላ ነበር።
ፌንግ አርዩ 3-100 ድሮን 10 ሜትር የክንፍ ርዝማኔ ያላት ሲሆን፤ በጋዝ ሞተር አማካኝነት የምትንቀሳቀስና ጠቅላላ ክብደቷም (የተሞላባትን ነዳጅ ጨምሮ) 60 ኪሎ ግራም ነው።
ድሮኗ “ፌንግ አርዩ 3-100” የሚለውን ስያሜዋም የቻይና አቪዬሽን ኢንዱስትሪ አባት ከሚባሉት ከፌንግ ሩ ያገኘች እንደሆነም ተነግሯል።
እንደ ዩኒቨርሲቲው መረጃ ከሆነ ድሮኗን የሰራው የተማሪዎቹ ቡድን 25 ከተለያዩ የትምህርት ዘርፎች የተውጣጡ የቅድመ ምረቃ ተማሪዎችን ያቀፈ ነው። የተማሪዎቹ አማካኝ ዕድሜም ከ20 ዓመት በታች እንደሆነ ተገልጿል።