ቤጅንግ እና ዋሽንግተን፤ በአሜሪካ አላስካ ግዛት የስትራቴጂካዊ ውይይት ማድረጋቸውን የሁለቱ ሀገራት ባለስልጣናት አስታወቁ
የፕሬዝዳንት ሺ ጂን ፒንግ እና የጆ ባይደን አመራር ከፍተኛ ባለስልጣናት ያደረጉት ውይይትም “ገንቢ“ እና “የሁለቱንም ሀገራት ብሔራዊ ጥቅም ያስጠበቀ“ መሆኑም ተገልጿል፡፡
ይሁንና በቤጅንግ እና በዋሸንግተን መካከል አሁንም ልዩነቶች መኖራቸውን ከውይይቱ በኋላ ለመገናኛ ብዙኃን ይፋ የተደረገው መግለጫ ያመለከታል ብሏል ሲጂቲኤን፡፡ የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ እና የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በስልክ ከተነጋገሩ በኋላ የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ አመራሮች የገጽ ለገጽ ውይይት ሲያደርጉ ይህ የመጀመሪያቸው ነው፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን “የቻይና አምባገነን አመራር በሀገር ቤትና በውጭ ሀገራት የሚፈጽማቸው ድርጊቶች አሳሳቢ ናቸው“ ሲሉ የቻይናው ኮሚኒስት ፓርቲ የውጭ ጉዳዮች ኃላፊ ያንግ በበኩላቸው “ቤጅንግ፣ በዋሸንግተን ላይ ብዙ ቅሬታዎች አሏት“ ብለዋል፡፡ የአሜሪካ ብሔራዊ የደህንነት አማካሪ ጃክ ሱሊቫን በበኩላቸው ከቻይና ጋር ጠንካራ ፉክክር እንጅ ግጭት እንደማያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡
የቻይናው ኮሚኒስት ፓርቲ የውጭ ጉዳዮች ኃላፊ ያንግ በበኩላቸው“አሜሪካ ለራሷ ዴሞክራሲ የምትለውን ነገር ልትወረውር ትፈልጋለች፤ በሀገር ቤት ግን ችግር አለባት፤ አሜሪካ ፣ ለቻይና ያላትን አመለካከት ማስተካከል አለባት“ ማለታቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ ቤጅንግ፤ ከዋሸንግተን የሚሰሙ ወቀሳዎችን እና ቅሬታዎችን እንደማትቀበል ገልጻለች፡፡
ከሰሞኑ በጃፓን እና በደቡብ ኮሪያ ጉብኝት አድርገው የተመለሱትና ከቻይና ልዑክ ጋር ውይይት ያደረጉት የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን፤ የቻይና አቋም ከኮሪያ እና ከጃፓን እንደሚለይ መገንዘባቸውን አስታውቀዋል፡፡