ቻይና ስር የሰደደ ድህነትን ሙሉ በሙሉ ማስወገዷን አስታወቀች
ባለፉት ስምንት ዓመታት በየዓመቱ በአማካይ ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ስር ከሰደደ ድህነት መላቀቃቸው ተገልጿል
በሀገሪቱ ባለፉት 40 ዓመታት 770 ሚሊዮን ዜጎችን ድህነትን ድል መንሳታቸውን ፕሬዝደንት ዢ ተናግረዋል
የቻይናው ፕሬዝደንት ዢ ጂንፒንግ ዛሬ ሐሙስ እለት ቤጂንግ በተካሄደው ብሔራዊ የምስጋና ኮንፈረንስ ላይ ባደረጉት ንግግር ፣ ቻይና ስር የሰደደ ድህነትን ማስወገዷን አስታውቀዋል፡፡
እንደዚህ ባሉ ስኬቶች 1.4 ቢሊዮን ያህል ህዝብ ያላት ቻይና “በታሪክ ተመዝግቦ የሚቀመጥ” ሌላ “ተዓምር” ፈጥራለች ሲሉ ዢ ተናግረዋል፡፡ ከድህነት መላቀቅ የመጨረሻ ግብ ሳይሆን የአዲስ ሕይወት እና አዲስ ጥረት መነሻ ነው ሲሉም አክለዋል፡፡
ዢ በማዕከላዊ ቻይና ሁናን ግዛት በተደረገ የጥናት ላይ ነበር እ.ኤ.አ ህዳር 2013 “ዓላማ ተኮር የድህነት ቅነሳ” የሚለውን ፅንሰ ሀሳብ ያቀረቡት፡፡
የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ (ሲ.ፒ.ሲ) ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ የህዝቦችን የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል እየሰራ ሲሆን ባለፉት ስምንት ዓመታት ደግሞ የሲ.ፒ.ሲ ማዕከላዊ ኮሚቴ በሀገሪቱ አስተዳደር ውስጥ ድህነትን የማስወገድ ጉልህ ስፍራ መያዙን ፕሬዝደንት ዢ ተናግረዋል፡፡
እ.ኤ.አ. በ 2012 ከተካሄደው 18ኛው የሲ.ፒ.ሲ ብሔራዊ ጉባዔ ወዲህ በየዓመቱ በአማካይ ከ 10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከድህነት መውጣታቸው ተጠቅሷል፡፡
በእነዚህ ስምንት ዓመታት ውስጥ አሁን ባለው መለኪያ ከድህነት ወለል በታች የሚኖሩት የመጨረሻው 98.99 ሚሊዮን የገጠር ነዋሪዎች ከድህነት ተላቀዋል ሲጂቲኤን እንደዘገበው፡፡ በድህነት ስር የነበሩ ሁሉም 832 ወረዳዎች እና 128,000 መንደሮች ከድህነት ዝርዝር ውስጥ ተሰርዘዋል፡፡
በተጨማሪም በአሁኑ የድህነት ወለል መለኪያ መሠረት ሲሰላ ከ 40 ዓመታት በፊት የተሃድሶ ሥራ ከጀመረ ወዲህ 770 ሚሊዮን የገጠር ነዋሪዎች ድህነትን አንበርክከዋል ነው ያሉት የቻይናው ፕሬዝደንት፡፡ በ40 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ከድህነት የወጡ ቻይናውያን ቁጥር ፣ በዚሁ ጊዜ በአጠቃላይ በዓለም ከድህነት ከተላቀቀው 70 በመቶውን ይሸፍናል፡፡
ቻይን ላለፉት ስምንት ዓመታት ወደ 1.6 ትሪሊዮን ዩዋን የሚጠጋ የበጀት ገንዘብ (246 ቢሊዮን ዶላር ገደማ) ሙሉ በሙሉ ለድህነት ቅነሳ ኢንቨስት ያደረገች ሲሆን ድህነትን በልማት ለማስወገድ ጥረት በማድረግ ላይ ያነጣጠረ የድህነት ቅነሳ ስትራቴጂን ተግባራዊ አድርጋለች፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በስምንት ዓመት ቆይታ ከ 1,800 በላይ ሠራተኞች ለሀገሪቱ ድህነት ቅነሳ ሲሰሩ ህይወታቸውን እንዳጡ ዢ አክለው ገልጸዋል፡፡
“ሀገሪቱ በድህነት ቅነሳ ‘የቻይና ምሳሌ’ በመፍጠር ለዓለም ድህነት ቅነሳም ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክታለች፡፡” ሲሉም ነው ዢ የተናገሩት፡፡