ቤጂንግና ኒውዴልሂ ከ”ጥርጣሬ መውጣት አለባቸው”- የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
ይህ የተባለው የቻይናና የህንድ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በተወያዩበት ወቅት ነበር
በድንበር ጉዳይ በተለያየ ጊዜ ግጭት ውስጥ የሚገቡት ህንድና ቻይና እርስበእርሳቸው መጠራጠር ማቆም እንዳለባቸው የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገለጹ
በድንበር ውዝግብ ጦር እስከመማዘዝ ደርሰው የነበሩት ቻይና እና ሕንድ ከ”ጥርጣሬ” እና ከ”አለመተማመን” ወጥተው ትክክለኛውን የወዳጅነት መንገድ መከተል እንዳለባቸው የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገለጹ፡፡
ሚኒስትሩ ዋንግ ይ ከሕንዱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሱብራህማንያም ጃይሻንካር ጋር በስልክ በተወያዩበት ወቅት በሁለቱ ጎረቤት ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት መተማመን እና መተባበርን የተከተለ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ቤጄንግ እና ኒውደልሂ “ትክክለኛውን የወዳጅነት መንገድ መከተል አለባቸው”ያሉት ሚኒስትሩ ጥርጣሬና አለመተማመን ወደኋላ ስለሚጎትቱ እነሱን ማስወገድ ይገባል ብለዋል፡፡
ግንኙነቱ የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ባስቀመጧቸው ስትራቴጅካዊ መንገዶች መሰረት መካሄድ እንዳለባቸውም ያነሱት የቻይናው ሹም የሁለትዮሽ ግንኙነቱ ወደአላስፈላጊ ሁኔታ እንዳይሄድ ሁለቱ ሀገራቱ ያላቸውን የድንበር ችግር በአግባቡ መፍታት አለባቸው ብለዋል፡፡ሚኒስትሩ የድንበር ላይ ውዝግቡ መፍትሄ ማግኘት እንዳለባቸው ገልጸው ይህ ግን የቻይና እና ሕንድን ግንኙነት አጠቃላይ ታሪክ እንደማያሳይ አስታውቀዋል፡፡
በቻይና እና ሕንድ ድንበር አካባቢዎች ላይ ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት የተፈጠረውን ነገር በተመለከተ ካለፉት ጊዜያት ትምህርቶችን በመውሰድ መፍታት እንደሚገባ አንስተዋል፡፡ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሕንድ በቻይና ላይ የያዘችው ፖሊሲ መወላወል ያለበትና የቤጅንግንና የኒውዴልሂን ጥቅም ያላገናዘበ ነው ብለዋል የቻይናው ሚኒስትር፡፡