በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የቻይና የጋብቻና የወሊድ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱ ተገለፀ
ቻይና “የአንድ ልጅ ፖሊሲን” ተግባራዊ አድርጋ በቆየችበት ወቅት የህዝቧ ቁጥር መቀነሱ ይታወቃል
የ“ዜሮ-ኮቪድ ፖሊሲ” በቻይናውያን ልጅ የመውለድ ፍለጎት ላይ ጉዳት አድርሷል
የኮቪድ-19 መከሰት የጋብቻ እና የወሊድ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ አስተዋጽኦ እንዳደረገ የቻይና ብሄራዊ ጤና ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ “ኮሮና ቫይረስ በአንዳንድ ሰዎች ጋብቻ እና ልጅ መውለድ ላይ ግልጽ ተጽዕኖ አሳድሯል” ብሏል።
ኮሚሸኑ የወረርሺኙ መስፋፋት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለልጆቻቸውን ትምህርት በሚከፍሉት ክፍያና የኑሮ ውድነት ተማረው የነበሩ ቻይናውያን የጋብቻ እቅዳቸውን እንዲያራዝሙ ምክንያት እንደሆነም ገልጿል፡፡
ብዙ ሴቶች ለማግባት ወይም ልጅ የመውለድ እቅዳቸውን ማዘግየታቸውን ቀጥለዋል ያለው ኮሚሽኑ፤ በሀገሪቱ አየተስተዋሉ ያሉ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እድገቶች ወደ "ጥልቅ ለውጦች" እያመሩ ነው ማለቱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ቻይና በሰዎች ህይወት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ማንኛውንም ወረርሽኞችን በፍጥነት ለማስወገድ በሚል ተግባራዊ ያደረገችው የ“ዜሮ-ኮቪድ ፖሊሲ” የሀገሪቱ ዜጎች ልጅ የመውለድ ፍላጎት ላይ ከፍተኛና ዘላቂ ጉዳት ማድረሱን የስነ-ህዝብ ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣል።
ባለው ሁኔታ በቻይና ውስጥ አዲስ የሚወለዱ ህፃናት በዚህ ዓመት ወደ ዝቅተኛ ደረጃ ይወርዳልም ነው ያሉት ባለሙያዎቹ፡፡
ባለሙያዎቹ፤ “ ካለፈው ዓመት 10 ነጥብ 6 ሚሊዮን ሕፃናት ጋር ሲነጸጸር ከ10 ሚሊዮን በታች ቅናሽ ያሳየ ሲሆን፤ ይህ ደረጃ በ2020 ከነበረው በ11 ነጥብ 5 በመቶ ያነሰ ነው” ብለዋል።
ቻይና እንደፈርንጆቹ በ2021 1 ነጥብ 16 በመቶ የወሊድ መጠን ነበራት፣ ይህም በዓለም ላይ ካሉት ዝቅተኛው ተመኖች አንዱ እና በዓለም አቀፍ መመዘኛዎች ለተረጋጋ ህዝብ አስፈላጊ እንደሆነ ከሚመከረው የ2 ነጥብ 1 በመቶ በታች ነው።
ቻይና እንደፈረንጆቹ ከ1980 እስከ 2015 የአንድ ልጅ ፖሊሲን ተግባራዊ ባደረገችበት ወቀት የሀገሪ ህዝብ ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱን ማመኗ የሚታወቅ ነው፡፡
ይህም ታዲያ ሀገሪቱ አረጋውያንን የመክፈል እና የመንከባከብ አቅሟን የሚፈትንና ቀውስ ሊስከትል የሚችል እንዳይሆን ተሰግቷል፡፡
ሁኔታው ያሰጋት ቻይናም ችግሩን ለመቋቋም በሚል በማዕከላዊና የተለያዩ ግዛቶች ባለስልጣናት አማካኝነት ከባለፈው ባለፈው አንድ አመት ጀምሮ እንደ የግብር እፎይታ፣ ረዘም ያለ የወሊድ ፈቃድ፣ የተሻሻለ የህክምና መድን፣ የመኖሪያ ቤት ድጎማ እና ለሶስተኛ ልጅ ተጨማሪ ገንዘብ የመሳሰሉ እርምጃዎችን ማስተዋወቅ ጀምራለች፡፡