ዩኤኢ የቻይናው ሲኖፋርም ክትባት ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቀደች
የበለጸጉ ሀገራት ለክትባቱ በመሽቀዳደም ላይ ሲሆኑ በድሀ ሀገራት የመከተብ እድል ያላቸው 1 በመቶ ብቻ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል
ክትባቱ ኮሮናቫይረስን ለመከላከል 86 በመቶ ውጤታማ መሆኑ ተገልጿል
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የቻይናው ሲኖፋርም ክትባት ከ 3ኛ ደረጃ ሙከራ በኋላ 86 በመቶ ኮሮናቫይረስን ለመከላከል ውጤታማ መሆኑን በማረጋገጥ ጥቅም ላይ እንዲውል ወስናለች፡፡
የሀገሪቱ የጤና ጥበቃና በሽታ መከላከል ሚኒስቴር ረቡዕ ዕለት ከቻይናው የመድኃኒት አምራች ጋር በመነጋገር “ዓለም አቀፉን ወረርሽኝን ለመዋጋት እንደ ትልቅ እርምጃ በመውሰድ” ክትባቱን ለመጠቀም እንደተወሰነ ገልጿል፡፡
ሚኒስቴሩ እና የአቡ ዳቢ ጤና ዲፓርትመንት በሰጡት ገለጻ ክትባቱ 99 በመቶ የፀረ እንግዳ አካላትን እንደሚያበለጽግ እና “መካከለኛ እና ከባድ በሽታዎችን ለመከላከል” መቶ በመቶ ውጤታማ መሆኑን ይፋ አድርገዋል፡፡
በተጨማሪም ክትባቱ ምንም ዓይነት የከፋ የደህንነት ስጋት እንደሌለው ገለጻው ያሳያል፡፡
ይህ የሲኖፋርም ክትባት በዩኤኢ በስፋት ሙከራ የተደረገለት ሲሆን 31,000 ሰዎች ክትባቱን በሙከራው ሂደት ወስደዋል፡፡ በባህርሬን እና ዮርዳኖስም አነስተኛ ሙከራዎች ተደርገዋል ሲል ዘ ናሺናል ዘግቧል፡፡
የክትባቱ ባለቤት ከቻይና ትላልቅ የመድሃኒት አምራች ኩባንያዎች አንዱ የሆነው የቤጂንግ ባዮሎጂካል ምርቶች ኢንስቲትዩት-ሲኖፋርም ነው፡፡
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ባለፈው መስከረም ወር ክትባቱ ለአስቸኳይ ጊዜ አገልግሎት ጥቅም ላይ እንዲውል ፈቃድ የሰጠች ሲሆን ከዚያን ጊዜ አንስቶ ለግንባር ቀደምት የህክምና ሰራተኞች ፣ ለመንግስት የጤና ባለስልጣናት ፣ ለአስቸኳይ ጊዜ አገልግሎት ሰራተኞች እንዲሁም ለዱባይ ምክትል ፕሬዝዳንት እና ገዥ ሼህ መሀመድ ቢን ራሺድ እንዲሁም ለሌሎች በርካታ ከፍተኛ የሀገሪቱ ባለስልጣናት ተሰጥቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት የበለጸጉ ሀገራት ለኮሮና ክትባት በሩጫ ላይ የሚገኙ ሲሆን ከአምራቾች ጋር በርካታ ውሎችን በመፈጸምም ላይ ናቸው፡፡ በርካታ በኢኮኖሚ የበለጸጉ በርካታ ሀገራት ዜጎቻቸውን በሙሉ ቢያንስ ለሦስት ጊዜያት ለመከተብ የሚያስችል መድሃኒት ለመግዛት ውል መፈጸማቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ከነዚህም ካናዳ እያንዳንዱ ዜጋዋ አምስት ዙር ሊደርሰው የሚችል ክትባት ለመግዛት ውል ፈጽማለች፡፡ ዩይትድ ኪንግደም ፊዘር የተሰኘውን ክትባት ከትናንት ህዳር 29 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ለዜጎቿ መስጠት ጀምራለች፡፡ የአሜሪካው ተመራጭ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በስልጣናቸው 100 ቀናት 100 ሚሊዮን ዜጎች ክትባት እንዲያገኙ ለማድረግ አቅደዋል፡፡
በተቃራኒው የአለማችን 70 ድሀ ሀገራት ክትባቱ ዘግይቶ ቢደርሳቸው እንኳን ከ10 ዜጎቻቻው አንዱን ብቻ ተጠቃሚ ሊያደርግ እንደሚችል ነው የሚጠበቀው፡፡