ቻይና የታይዋንን ነጻነት የሚያቀነቅኑ ግለሰቦችን በሞት እቀጣለሁ ስትል አስፈራራች
ህጉ ታይዋን የምትገነጠል ከሆነ ወይም የምትሞክር ከሆነ፣ ቻይና እርምጃ እንድትወስድ እንደህጋዊ መሰረት ያገለግላታል ተብሏል
የታይዋን ሜይንላንድ ጉዳይ ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ ማንም ዜጋ በቻይና ማስፈራሪያ ስጋት እንዳይገባው አሳስቧል
ቻይና የታይዋንን ነጻነት የሚያቀነቅኑ ግለሰቦችን በሞት እቀጣለሁ ስትል አስፈራራች።
የቻይና ፍርድ ቤቶች በዲሞክራሲያዊቷ ደሴት ግዛት ውስጥ የመዳኘት ስልጣን ባይኖራቸው፣ ቻይና የታይዋንን ነጻነት የሚያቀነቅኑ ተገንጣዮችን በሞት እንደምትቀጣ በዛሬው እለት አስፈራርታለች።
ታይዋንን እንደሉአላዊ ግዛቷ የምትቆጥራት ቻይና፣ ባለፈው ወር ስልጣን የያዙት ፕሬዝደንት ላይኢ ቺንግ-ቲ የተገንጣይ ሀሳብ አራማጅ ናቸው በማለት እንደማትወዳቸው ግለጽ አድርጋለች፤ ፕሬዝደንቱ በዓለ ሲመታቸውን ከደረጉ በኋላ ወዲያውኑ ወታደራዊ ልምምድ አድርጋለች።
ታይዋን፣ ፕሬዝደንት ቺንግ-ቲ ስልጣን ከያዙ ወዲህ ቻይና ጫና እየጨመረች ነው የሚል ቅሬታ እያቀረበች ነው።
እንደ ሽንዋ ዘገባ ከሆነ አዲሱ መመሪያ የቻይና ፍርድ ቤቶች፣ አቃቤ ህጎች፣ የህዝብ እና የመንግስት የጸጥታ አካላት "ሀገሪቱን በሚከፋፍሉ፣ መገንጠልን በሚያቀነቅኑ ላይ ከባድ ቅጣት በማሳረፍ ሉአላዊነትን እና የግዛት አንድነትን ማስጠበቅ ይኖርባቸዋል።"
ይህ መመሪያ በፈረንጆቹ 2005 የወጣውን የጸረ- መገንጠል ህግ ጨምሮ ከዚህ በፊት ከወጡ ህጎች ጋር የሚናበብ መሆኑን ዘገባው ጠቅሷል።
ህጉ ታይዋን የምትገነጠል ከሆነ ወይም የምትሞክር ከሆነ፣ ቻይና እርምጃ እንድትወስድ እንደህጋዊ መሰረት ያገለግላታል ተብሏል።
በቻይና ፐብሊክ ሴኩሪቲ ሚኒስቴር የሚሰሩ ሰን ሰንግ የተባሉ ባለስልጣን እንደተናገሩት "በመገንጠል ወንጀል" ላይ የሚተላለፈው የመጨረሻው ቅጣት የሞት ቅጣት ነው።
የታይዋን ሜይንላንድ(ቻይና) ጉዳይ ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ የቤጂንግን ውሳኔ አውግዘው፣ ማንም ዜጋ በቻይና ማስፈራሪያ ስጋት እንዳይገባው አሳስቧል። "የቤጄንግ ባለስልጣናት በታይዋን ላይ ምንም ስልጣን የላቸውም ፤ ህዝባችን የቻይና ኮሚኒስት ህግ እና እሴት ተገዥ አይሆንም። መንግስት ህዝቡ በቻይና ኮሙኒስት ፓርቲ ስጋት እንዳይገባው ጠይቋል" ብለዋል መግለጫው።
በአዲሱ መመሪያ መሰረት ታይዋንን እንደሀገር ወደ አለምአቀፍ ድርጅቶች ማስገባት፣ ይፋዊ የውጭ ግንኙነት ማድረግ፣ ውህደትን የሚያቀነቅኑ ቡድኖችን፣ ሰዎችን እና ፓርቲዎችን መጨቆን ሊያስቀጡ ከሚችሉት ወንጀሎች ውስጥ ይጠቀሳሉ።