ቤጂንግ አዲሱን የታይዋን ፕሬዝዳንት “አደገኛ አስገንጣይ” ናቸው በሚል ትወቅሳለች
የአሜሪካ የጦር መርከብ በጠባቡ የታይዋን ሰርጥ በኩል ማለፍ ቻይናን አስቆጥቷል።
ታይዋን የግዛቴ አካል ናት የምትለው ቤጂንግ በመተላለፊያ ሰርጡ የማዘዝ መብቱም የራሷ መሆኑን ትገልጻለች።
አሜሪካ በበኩሏ የታይዋን ሰርጥ ነጻና ማንም በባለቤትነት የሚያዝበት አለመሆኑን ትሞግታለች፤ በወር አንዴ የጦር መርከብና አውሮፕላኖቿ በታይዋን ሰርጥ ቅኝት እንዲያደርጉም ታደርጋለች።
የትናንቱ ቤጂንግን ይበልጥ ያበሳጨው ግን አዲሱ የታይዋን ተመራጭ ፕሬዝዳንት በዓለ ሲመት ሊደረግ በተቃረበበት ወቅት መካሄዱ ነው ይላል የሬውተርስ ዘገባ።
ቻይና “አደገኛ አስገንጣይ” ስትል የምትገልጻቸው ተመራጩ ፕሬዝዳንት ላይ ቺንግ ቲ ከ11 ቀናት በኋላ በዓለ ሲመታቸው ይካሄዳል።
በዚህ የአካባቢው ውጥረት በተባባሰበት ወቅት ዋሽንግተን “ዩኤስኤስ ሃስሊ” የተሰኘችውን የጦር መርከብ ወደ ታይዋን ሰርጥ መላኳ በቻይና “ጸብ አጫሪ” ድርጊት ሆኖ ተቆጥሯል።
የቻይና የመከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የአሜሪካ መርከብ ከታይዋን ሰርጥ እስክትወጣ ድረስ መርከቦችና የጦር አውሮፕላኖች ሲከታተሏት ነበር ብሏል።
የሀገሪቱ ጦር በታይዋን ሰርጥ አካባቢ ያለውን ሁኔታ በተጠንቀቅ እየተከታተለ መሆኑንም ነው ያስታወቀው።
የታይዋን መከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ የአሜሪካ የጦር መርከብ በታይዋን ሰርጥ ያደረገችውን ጉዞ የራስ ገዝ ደሴቷ ሃይሎች መከታተላቸውንና የተለየ አዲስ ጉዳይ አለማጋጠሙን አስታውቋል።
የታይፒ አስተዳደር ቤጂንግ የምታነሳውን የሉአላዊ ግዛት አካልነት ጉዳይም ውድቅ አድርጓል፤ የደሴቷን ቀጣይ እጣ ፈንታ የሚወስኑት ነዋሪዎቿ ናቸው ብሏል።
የአሜሪካ የጦር መርከብ እንቅስቃሴና የተመራጩ ፕሬዝዳንት በዓለ ሲመት መቃረብን ተከትሎ የቤጂንግ የጦር አውሮፕላኖች በታይዋን የአየር ክልል የሚያደርጉት በረራ መጠናከሩ ተገልጿል።