ፕሬዝዳንት ሺ “ታይዋንን ከቻይና ለመነጠል የሚደረግ ማንኛውንም ሙከራ እናስቆማለን” አሉ
ታይፒ ከቤጂንግ ጋር ያላትን ግንኙነት ይወስናል የተባለ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ከሁለት ሳምንት በኋላ ታደርጋለች
ታይዋን ከምዕራባውያን ጋር የመሰረተችው ወዳጅነት በቻይና የሚወደድ አልሆነም
የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግ “ታይዋንን ከቻይና ለመነጠል የሚደረግ ማንኛውንም ሙከራ እናስቆመዋለን” ሲሉ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ ይህን አስተያየት የሰጡት ታይዋን ከሁለት ሳምንት በኋላ ለምታደርገው ፕሬዝዳንታዊ እና የፓርላማ አባላት ምርጫ የደሴቷ ቀጣይ እጣ ፈንታ የምርጫ ቅስቀሳ አካል መሆኑን ተከትሎ ነው።
የታይዋን ምርጫ የውስጥ ጉዳዬ ነው ያለችው ቤጂንግ በፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ሰፊ የማሸነፍ እድል ያላቸውን የዴሞክራቲክ ፕሮግረሲቭ ፓርቲ ተወካይ ላይ ቺንግቲ “አደገኛ አስገንጣይ” ናቸው በሚል አውግዛቸዋለች።
የገዥው ዴሞክራቲክ ፕሮግረሲቭ ፓርቲ ዋነኛው ተቀናቃኝ ኩሚንታንግ ፓርቲም ከቻይና ጋር ጥብቅ ወዳጅነት መመስረትን የሚደግፍ ቢሆንም የደሴቷ እጣፈንታ በህዝቦቿ ይወሰናል የሚል አቋም ይዟል።
ከሁለት ሳምንት በኋላ በሚደረገው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አሸንፎ ስልጣን የሚይዘው አካል ከቤጂንግ ጋር መፋጠጡ አይቀርም የሚለው የሬውተርስ ዘገባም፥ በታይዋን ሰርጥ ዳግም ውጥረት ሊነግስ እንደሚችል ጠቁሟል።
ፕሬዝዳንት ሺ ጂንፒንግም “የታይዋን እና ቻይና ውህደት አይቀሬ ነው፤ ታይፒን ከእናት ሀገሯ የመነጠል ሙከራንም እንከላከላለን” ማለታቸውን ሽንዋ ዘግቧል።
ቤጂንግ እንደሉአላዊ የግዛቷ አካል የምትቆጥራትን ታይፒ ለመገንጠል የሚደረጉ ሙከራዎችን በሃይል ልታስቆም እንደምትችል ግን አልጠቀሱም።
ባለፉት 18 ወራት ሁለት ግዙት ወታደራዊ ልምምዶችን በታይዋን አቅራቢያ ያደረገችው ቻይና፥ ወደ ታይዋን ሰርጥ የጦር አውሮፕላኖቿን እና መርከቦቿን ስትልክ ሰንብታለች።
ታይፒ እንደ ሉአላዊ ሀገር ከአሜሪካ እና ሌሎች ምዕራባውያን ሀገራት ጋር ወታደራዊ ግንኙነት ለመመስረት መሞከሯና ዋሽንግተን ለደሴቷ የጦር መሳሪያ ለመሸጥ መስማማቷ ውጥረቱን ማባባሱም ይታወሳል።