ቻይና ፤ በታይዋን ስትሬት በሚገኘው የአሜሪካ ባህር ኃይል እንቅስቀሴ ላይ ክትትል እያደረኩ ነው አለች
የቻይና የመከላከያ ሚኒስትር ቻይና በታይዋን ጉዳይ ማንኛውም ኃይል እንደማትታገስ ማስጠንቀቃቸው አይዘነጋም
የቻይና የመከላከያ ሚኒስትር ቻይና በታይዋን ጉዳይ ማንኛውም ኃይል እንደማትታገስ ማስጠንቀቃቸው አይዘነጋም
አሜሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለት የባህር ኃይል መርከቦች ወደ ታይዋን ዳርቻ መላኳ የአሜሪካ ባህር ኃይል ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በዚህ ስጋት የገባት ቻይና ፤ ወደ ታይዋን ባቀናው የአሜሪካ የባህር ኃይል ላይ ጥብቅ ክትትል እያደረገች መሆኗ ገልጻለች፡፡
የቻይና ጦር “በቤጂንግ ላይ ሊቃጣ የሚችል ማንኛውም ትንኮሳ ለመመከት ዝግጁ ነኝ” ማለቱም ነው የሮይተርስ ዘገባ የሚያመለከተው፡፡
የቻይና የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት፤ አሜሪካ ጸብ አጫሪ ድርጊት ከፈጸመች ቻይና አስፈላጊውን ወታደራዊ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆኗ ከቀናት በፊት ማስታወቁ አይዘነጋም፡፡
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ዋንግ ዌንቢን ዛሬ በመግለጫቸው አሜሪካ፤ ቻይናን ለመያዝ ታይዋንን ከመጠቀም እንድትቆጠብ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡
ቻይና በታይዋን ጉዳይ እንደማትደራደርና ውጊያ መግጠም ካለባትም ለመግጠም ዝግጁ መሆኗን የቻይና የመከላከያ ሚኒስትር ዌዪ ፈንጊሄ ከአሜሪካው አቻቸው ሎልዩድ አውስቲን ጋር ከአንድ ወር በፊት በኢስያ የደህንነት ጉባዔ ላይ በነበራቸው የጎንዮሽ ውይይት መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
በውይይቱ ወቅትም የቻይናው መከላከያ ሚኒስትር ዌዪ ፈንጊሄ፤ ታይዋንን ከቻይና መገንጠል የቻይና ወታደር “ማንኛውንም አይነት ዋጋ በመክፈል ከመዋጋት ውጭ ምርጫ እንዳይኖረው ያደርጋል” ብለዋል።
“ህዝባዊ ነፃ አውጪ ጦር” በመባል የሚጠራው የቻይና ጦር የሀገሩን ብሔራዊ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነትን ከማስጠበቅ በቀር ሌላ ምርጫ እንደማይኖረውም ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
ቻይና እና ከአሜሪካ ጋር ወታደራዊ ትብብርን ጨምሮ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያም ንግግርና ውይይት የነበራት ቢሆንም በፔሎሲ ጉብኝት ምክንያት ሁሉንም ላለማድረግ ውሳኔ ማሳለፏን ማሳወቋ ይታወሳል፡፡
ከዚህ ባለፈም የፕሬዝዳንት ዢ ሺን ፒንግ አስተዳደር፤ ሀገሪቱ ከአሜሪካ ጋር የነበራትን የድንበር አልባ ወንጀል መከላከል፣ ስደተኞችን የማጓጓዝ፣ አደገኛ ዕጽ ዝውውር መከላከል እና ሌሎች ስምንት የትብብር መስኮችን ማቋረጡን ገልጿል፡፡
ቻይናና አሜሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ የበላይነትን ለማስፈን ከሚደረግ ሽኩቻ ባለፈ በንግድና ኢኮኖሚ ላይ ያተኮረ እሰጥ አገባ የነበራቸው ቢሆንም ታይዋን ግን የሀገራቱን ግብ ግብ የበለጠ እንዲካረር አድርጋዋለች ተብሏል፡፡