ቻይና፤ አሜሪካ የሚመጡትን "ከባድ መዘዞች መቻል ይኖርባታል” ስትል ዛተች
የቻይና መከላከያ ሚኒስቴር “በታይዋን የባህር ወሽመጥ ላይ ላለው ውጥረት አሜሪካ ኃላፊነቱን ትወስዳልች” ብሏል
የፔንታጎን፣ የስቴት ዲፓርትመንት እና የዋይት ሀውስ ባለስልጣናት የቻይና እርምጃ “ኃላፊነት የጎደለው” ሲሉ በማውገዝ ላይ ናቸው
የፔሎሲ የታይዋን ጉብኝት እጅጉን ያስቆጣት ቻይና፣ አሜሪካ የሚመጡትን "ከባድ መዘዞች መቻል ይኖርባታል” ስትል ዛተች፡፡
የቻይና መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዉ ኪያን በኦን ላይን ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ፡ “በታይዋን የባህር ወሽመጥ ላይ ያለውን ውጥረት በትንኮሳ እንዲፈጠር ያደረገቸው አሜሪካ ናት፣ ስለዚህም አሜሪካ ለድረጊቷ ኃላፊነት በመውሰድ የሚከተሉ አስከፊ መዘዝ መሸከም ይኖርባታል” ብለዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የቻይና ወታደራዊ መርከቦች፣ አውሮፕላኖች እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች በደሴቲቱ እና በባህር ሃይሏ ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን የታይዋን የመከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።
“ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት” አውሮፕላኖችን እና መርከቦችን መላካቸውንም ጭምር አስታውቋል ታይዋን መከላከያ ሚኒስቴር፡፡
በፔሎሲ የታይዋን ጉብኝት የተቆጣችው ቻይና ለአሜሪካ ምላሽ ነው በሚል አስካሁን በታይፔ ላይ የባለስቲክ ሚሳኤሎችን የመተኮስ ሙከራዎች ከማድረግ በተጨማሪ ከአሜሪካ ጋር የነበሯት የመከላከያ ፖሊሲ ማስተባበሪያን እና የባህር ኃይል-ወታደራዊ ምክክርን ያካተቱ መደበኛ ንግግሮችን መሰረዟ ባሳለፍነው አርብ ይፋ አድርጋለች፡፡
የፔንታጎን፣ የስቴት ዲፓርትመንት እና የዋይት ሀውስ ባለስልጣናት የቻይና እርምጃ “ኃላፊነት የጎደለው” ነው ሲሉ አውግዘውታል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ፤ቻይና የሁለትዮሽ ግንኙነትን ለማቆም አደንዛዥ እጾች፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች እና የአየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ በስምንት ቁልፍ ጉዳዮች ላይ የወሰደችው አጸፋዊ እርምጃ፤ አሜሪካን ብቻ ሳይሆን ዓለምን የሚቀጣ ነው ሲሉ ከቀናት በፊት መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
ብሊንከን "የአየር ንብረት ትብብርን ማገድ አሜሪካን ብቻ ሳይሆን ዓለምን በተለይም በማደግ ላይ ያሉትን ሀገራት የሚቀጣ ነው።በሁለቱ ሀገራት መካከል ባለው ልዩነት ምክንያት ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ትብብሮችን እንደ መያዣ መጠቀም የለብንም" ሲሉ መደመጣቸውም ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ቻይና በታይዋን ዙሪያ እየፈጸመች ያለውን አደገኛና በቀጠናው አለመረጋጋት ሊፈጥር የሚችል ድርጊትን በተመለከተ ዋሽንግተን ከአጋሮቿ እየሰማች ነው ያሉት ብሊንከን ፤ “ ዋሽንግተን ጉዳዩን በምታስተናግድበት መንገድ እያስተናገደች ጸንታ ትቀጥላለች”ም ብለዋል ብሊንከን፡፡