ቻይና የኮሮና ወረርሽኝ መነሻዎችን የተመለከቱ መረጃዎችን ልትሰጥ ይገባል - ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም
ወረርሽኙ ከውሃን ቤተ ሙከራዎች ያመለጠ ነው በሚል ይነሳል ምንም እንኳን ለቻይና ባይዋጥላትም
ዶ/ር ቴድሮስ “ቻይና ግልጽ እና ተባባሪ” እንድትሆንም ጠይቀዋል
አድሃኖም ቻይና ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አመጣጥ ጋር የተያያዙ ጥሬ መረጃዎችን ልትሰጥ እንደሚገባ
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አመጣጥን ለማወቁ የተደረጉ ጥረቶች በመረጃ እጥረት ምክንያት መስተጓጎላቸውን የዓለም ጤና ድርጀት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ ተናገሩ፡፡
የድርጅቱ የምርመራ ባለሙያዎች ከቻይና ሳይንቲስቶች ጋር በመሆን ቫይረሱ ተነሳበት በሚባለው በውሃን ከተማና በአካባቢው ለአራት ሳምንታት የዘለቀ ምርመራ አድርገዋል፡፡
በምርመራቸው ቫይረሱ ምናልባትም በሌሎች እንስሳት በኩል ከሌሊት ወፎች ወደ ሰው ሳይተላለፍ አልቀረም የሚል ሪፖርትን ነበር የሰጡት፡፡
ከቤተ ሙከራ (ላቦራቶሪ) ያመለጠ ነው በሚል የሚነሳው እምብዛም የማይመስል ነገር ነው በሚልም ነበር ሪፖርት የተደረገው፡፡
ሆኖም አሜሪካን መሰል ሌሎች ሃገራት በሪፖርቱ ደስተኛ አይደሉም፡፡
በዚህም ዶ/ር ቴድሮስ “ቻይና ግልጽ እና ተባባሪ እንድትሆን እንጠይቃለን” ሲሉ ዛሬ በነበራቸው ጋዜጣዊ መግለጫ ጠይቀዋል፡፡
በበሽታው ለተጠቁ እና ለሞቱ ምን እንደተፈጠረ የማሳወቅ ግዴታ አለብን ሲሉም ነው ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት፡፡
ቻይና ቫይረሱ “ከውሃን ቤተ ሙከራዎች ያመለጠ ነው” መባሉን ስታስተባብል ቆይታለች፡፡ ጉዳዩን ፖለቲካዊ መልክ ማላበስ የምርመራ ሂደቱን ይጎዳዋል ስትልም ነበር የቆየችው፡፡
ዶ/ር ቴድሮስ ነገ አርብ የምርመራውን 2ኛ ምዕራፍ በተመለከተ ለድርጅቱ 194 አባል ሃገራት ማብራሪያ ይሰጣሉ፡፡
ከቻይና ውሃን ተነሳ የሚባልለት የኮሮና ቫይረስ እስካሁን ከ4 ሚሊዬን የሚልቁ ሰዎችን ህይወት መቅጠፉ እና ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ማስከተሉ የሚታወቅ ነው፡፡