ክትባቱን መቃወም መንግስት ትምህርት ቤቶችን ለመክፈትና ጤናማ ለማድረግ የጀመረውን እርምጃ ያሰናክለዋል ተብሏል
በደቡብ አፍሪካ ጋውተንግ ግዛት መምህራንና ድጋፍ ሰጭ ሰራተኞች የኮሮና ቫይረስ ክትባትን ለመውሰድ ፈቃዳ አለመሆናቸው ተገለጸ፡፡
በግዛቲቱ እስከ 10 ሺ የሚሆኑ መምህራንና የድጋፍ ሰጭ ሰራተኞች ክትባቱን መቃወማቸውን ጂቲኤን ዘግቧል፡፡ አንዳንድ ባለስልጣንት ክትባቱን የተቃወሙት 9 ሺ 113 መሆናቸውን ሲገልጹ ሌሎች ደግሞ 10 ሺ ናቸው ብለዋል፡፡
የግዛቲቱ የትምህርት ሥራ አስፈፃሚ አባል ፓንያዛ ሌሱፊ፤ ክትባቱ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ቢሆንም የዓለም ጤና ድርጅት ግን ለቫይረሱ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች እንዲከተቡ እንደሚያበረታታ ተናግረዋል፡፡
ይሁንና 10 ሺ የሚሆኑ ባለሙዎች በአንድም በሌላም ምክንያት እስካሁን ክትባቱን እየተቃወሙ ነው ብለዋል፡፡
በደቡብ አፍሪካ ጋውተንግ ግዛት የትምህርት ቃል አቀባይ ስቲቭ ማቦና መምህራንን እና ደጋፍ ሰጭ ሰራተኞች ክትባቱን እንዲወስዱ ጠይቀዋል፡፡
ክትባቱን መቃወም መንግስት በዚህ የወረርሽኝ ወቅት ትምህርት ቤቶችን ለመክፈትና ጤናማ ለማድረግ የጀመረውን እርምጃ እንደሚያሰናክልም ተገልጿል፡፡
ደቡብ አፍሪካ በአሁኑ ወቅት መምህራንን እና የድጋፍ ሰጭ ሰራተኞችን እየከተበች ሲሆን፤ የፖሊስና መከላከያ አባላት ደግሞ ከሰኞ ጀምሮ ክትባት እንደሚወስዱ ይጠበቃል ተብሏል፡፡
በሀገሪቱ ቫይረሱ በከፍተኛ መጠን በመስፋፋቱ በተለይ ጆሃንስበርግ ያሉ ሆስፒታሎች ተጨናንቀዋል፤የጤና ባለሙያዎችም በጹኑ ለታመሙ ታካሚዎች በቂ አልጋ ለማግኘት መቸገራቸውን ገልጸዋል፡፡
የደቡብ አፍሪካ የህክምና ባለሙያዎች ማህበር የህክምና ባለሙያዎች እጥረት ባለበት ሁኔታ መንግስት 200 የሚሆኑ ባለሙያዎችን ባለመመደቡ መንግስትን እከሳላሁ ሲል አስጠንቅቋል፡፡