ቻይና ወደ ጨረቃ ደቡባዊ ዋልታ የላከቻት መንኮራኩር በተሳካ ሁኔታ አረፈች
“ቻንግኢ-6” የሚል ስያሜ የተሰጣት መንኮራኩር አፈርና ማዕድናትን ሰብስባ ወደ መሬት ይዛ ትመለሳለች ተብሏል
ቤጂንግ በ2030 ጠፈርተኞችን ወደ ጨረቃ ለመላክ አቅዳለች
ቻይና ወደ ጨረቃ የላከቻት ሰው አልባ መንኮራኩር በተሳካ ሁኔታ ማረፏን ገለጸች።
“ቻንግኢ-6” የሚል ስያሜ የተሰጣት መንኮራኩር በጨረቃ ደቡባዊ ዋልታ “አትኪን” በተባለ ሸለቆ ማረፏን የቻይና ብሄራዊ የስፔስ አስተዳደር አስታውቋል።
በግንቦት ወር መጀመሪያ ተልዕኮዋን የጀመረችው “ቻንግኢ-6” በአጠቃላይ የ53 ቀናት ቆይታ ይኖራታል ተብሏል።
በቆይታዋም ከመሬት በተቃራኒ በሚገኘውና መሬት ላይ ሆኖ በማይታየው የጨረቃ ክፍል የሚገኙ ውድ ማዕድናትና አፈር በመሰብሰብ ወደ ምድር ይዛ ትመለሳለች ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ ተልዕኮ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው የተባለ ሲሆን፥ ቤጂንግ በቀጣይ ጠፈርተኞችን ወደ ጨረቃ ለመላክ የምታደርገውን ጥረት ስኬታማ ለማድረግ እንደሚያግዝም ታምኖበታል።
ቻይና በ2019 “ቻንግኢ- 4” መንኮራኩሯን በጨረቃ ደቡባዊ ዋልታ በማሳረፍ የመጀመሪያዋ ሀገር መሆኗ ይታወሳል።
ዛሬ በተሳካ ሁኔታ ማረፏ የተነገረላት “ቻንግኢ-6”ም ቻይና በህዋ ምርምር የበላይነት እንድትይዝ በሩን ልትከፍት እንደምትችል ተገምቷል።
ይሁን እንጂ መንኮራኩሯ ካረፈች በኋላ ያለውን እንቅስቃሴዋን መመልከት አዳጋች መሆኑ ነው የተነገረው። ጨለማና ሩቁ የጨረቃ ክፍል ላይ ያረፈችውን “ቻንግኢ-6” እንቅስቃሴ ለመመልከት ባለፈው መጋቢት ወር ወደ ጨረቃ የተላከች ሳተላይት ጥቅም ላይ እንደምትውል ተጠቅሷል።
4 ቢሊየን አመት እድሜ ካለው ሸለቆ 2 ኪሎግራም የሚጠጋ አፈርና ማዕድናትን ሰብስባ ወደመሬት ይዛ ትመለሳለች ተብላ የምትጠበቀው የቻይና መንኮራኩር ውስብስብ ሂደቶችን እንደምታልፍ ሽንዋ አስነብቧል።
ቻይና ሁለት መሰል ተልዕኮዎችን ለመፈጸምና በፈረንጆቹ 2030 ጠፈርተኞችን ወደ ጨረቃ ለመላክ ማቀዷን መግለጿ ይታወሳል።
የዛሬው የ”ቻንግኢ-6” ስኬታማ ጉዞም አሜሪካን ጨምሮ በርካታ ሀገራት ጨረቃን የማሰስ ፍላጎታቸው ይበልጥ እንዲጨምር ያደርጋል ተብሏል።
ህንድ ባለፈው አመት ለመጀመሪያ ጊዜ ጨረቃ ላይ በተሳካ ሁኔታ መንኮራኩሯን ማሳረፍ የቻለች ሲሆን፥ ሩሲያ በበኩሏ “ሉና 25” የተሰኘችው መንኮራኩሯ መከስከሷ ይታወሳል።
ጃፓን በጥር ወር 2024 በጨረቃ ላይ መንኮራኩር ያሳረፈች አምስተኛዋ ሀገር መሆኗም አይዘነጋም።