ምዕራባዊያን የሙስና ዘመቻው ለሀገሪቱ መሪ ታማኝ ያልሆኑ ወታደራዊ አመራሮችን ለመቀነስ አላማ ያደረገ ነው ብለዋል
ቻይና በመከላከያ ጦሯ ላይ የሙስና ዘመቻ መጀመሯ ተገልጿል።
የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሺ ዢንፒንግ በቻይና ተንሰራፍቷል የተባለውን ሙስና ለመቀነስ በተለያዩ ተቋማት ላይ የሙስና ዘመቻ መጀመራቸው ይታወሳል፡፡
በመከላከያ ጦሩ ላይ ተጀምሯል የተባለው አዲስ የሙስና ዘመቻ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮችን እና ጄነራሎችን ጭምር ተጠያቂ የሚያደርግ ነው ተብሏል፡፡ ሺ ዢንፒንግ የመከላከያው ዶግማ ፣ አሰራር እና ታማኝነት ከሙስና የተላቀቀ መሆኑን ማረጋገጥ ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
የጥይት ቃታ ለፓርቲው እና ለመንግስት ታማኝ በሆኑ ወታደሮች እጀ ብቻ ሊገኝ ይገባል ያሉት ፕሬዝዳንቱ የጦሩን አወቃቀር ከሙስና የጸዳ መሆኑን ለመረጋገጥ የሙስና ዘመቻዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ነው ያሉት፡፡
ባለፉት 10 በላይ አመታት ቻይና ጦሯን ዘመናዊ ትጥቅ እና ቴክኖሎጂ ለማስታጠቅ በምታደርገው ጥረት በነበሩ ግዢዎች ከፍተኛ ሙስና ታይቷል መባሉን ተከትሎ በተለያዩ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮች ላይ ምርመራ ስታደርግ ቆይታለች፡፡
ከባለፈው አመት ሀምሌ ወር አንስቶ በመካሄድ ላይ የሚገኘው የሙስና ዘመቻ የመከላከያ ሚንስትሩን ሊ ሻንግፉ እና የሮኬት ክፍለጦር አዛዡን ከስልጣን አንስቷል፡፡
የመከላከያ ሚንስትሩ በወታደራዊ ጦር መሳሪያዎች ግዢ ላይ በተፈጸመ ሙስና ተሳትፎ አላቸው በሚል የወንጀል ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል፡፡
አንዳንዶች ቻይና በአዲስ መልክ የዘመረችው የሙስና ዘመቻ ለቻይናው ኮሚኒስት ፓርቲ ታማኝ ያልሆኑ ጀነራሎችን ከስልጣን ገሸሽ ለማድረግ አላማ ያለው ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም በዚህ ሂደት ውስጥ ከፍተኛ ልምድ እና ማዕረግ ያላቸው የጦር መኮንኖች ከሀላፊነት መነሳት የጦሩን አቅም ሊጎዳው ይችላል ተብሏል፡፡
ከሙስና ጋር በተያያዘ በሚነሱ ጄነራሎች ምትክ የሚተኩ ወታደራዊ አመራሮች ልምድ ማነስ ደግሞ በጦሩ የመዋጋት አቅም ላይ ተጽዕኖ ሊኖረው እንደሚችልም ስጋት አለ ፡፡
ባለፈው አመት የመከላከያ ሚንስትሩ በሙስና ክስ ከስልጣን መነሳት በጦሩ መካከል መጠራጠር እና ክፍፍል አስነስቶ እንደነበር ያስታወሰው የቪኦኤ ዘገባ ዘመቻው ፓርቲው በጦሩ ላይ ያለውን ፍጹም የበላይነት ለማረጋገጥ የሚደረግ ነው በሚል በጦሩ መካከል ጉምጉምታን ፈጥሯል ነው ያለው፡፡