ደቡብ አፍሪካ ተፈጸመ ከተባለ የሙስና ቅሌት ጋር በተያያዘ የጤና ሚኒስትሯን በጊዜያዊነት አገደች
ተቋሙ በሚኒስትሩ የቅርብ ወዳጆችና ረዳቶች ባለቤትነት የሚተዳደር ስለመሆኑ ተገልጿል
ሚኒስትሩ የታገዱት ለአንድ ተቋም ከሰጡት ኮንትራት ጋር በተያያዘ
ደቡብ አፍሪካ ተፈጸመ ከተባለ የሙስና ቅሌት ጋር በተያያዘ የጤና ሚኒስትሯን ዶ/ር ዝዌሊ ሚኬዚ በጊዜያዊነት ከኃላፊነት አገደች፡፡
ሚኒስትሩ የታገዱት ‘ዲጂታል ቫይብ’ ከተባለ አንድ የግል ተቋም ጋር እ.ኤ.አ በ2019 ከፈጸሙት የ150 ሚሊዬን ራንድ የስራ ውል ስምምነት ጋር በተያያዘ ነው፡፡
‘ዲጂታል ቫይብ’ በሚኒስትሩ የቅርብ ወዳጆችና ረዳቶች ባለቤትነት የሚተዳደር የግል የኮሙኒኬሽን ስራዎች ተቋም ነው፡፡
ይህም ‘ኮንትራቱን የሰጡት ባላቸው ቅርበትና ትውውቅ ነው’ በሚል እንዲጠረጠሩ አድርጓል ፡፡
ዴይሊ ማቭሪክ የተሰኘው የሃገሪቱ ጋዜጣም ‘ዲጂታል ቫይብ’ በሚኒስትሩ ልጅ ከሚንቀሳቀሱ የንግድ ተቋማት በአንዱ 300 ሺ ራንድ አስተላልፏል ሲል ዘግቧል፤ ምንም እንኳን እርሳቸው ቢያስተባብሉም፡፡
ጥርጣሬው በገለልተኛ መርማሪ አካል እስኪጣራ ድረስም በልዩ ሁኔታ የዓመት ረፍት እንዲወጡ ተደርጓል፡፡
ረፍቱ ከፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ ጋር ተመካክረው ያገኙት ነው፡፡
ይህ መሆኑ የምርመራ ሂደቶችን በቅርበት ለመከታተል እንደሚያስችላቸው ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡
የቱሪዝም ሚኒስትሯ ማሞሎኮ ኩባዪ ንጉባኔ ሚኬዚን ተክተው በጊዜያዊነት ሚኒስቴሩን እንደሚመሩም ነው ፕሬዝዳንቱ ያስታወቁት፡፡
ሆኖም ምክትል የጤና ሚኒስትሩ እያሉ የቱሪዝም ሚኒስትሯ በጊዜዊነት ይተኳቸዋል መባሉ አግባብነት የለውም በሚል ብዙዎች የፕሬዝዳንቱን አካሄድ ተቃውመዋል፡፡
የሚኒስትሩ በጊዜያዊነት መታገድ በቂ እንዳልሆነ በማስታወቅም ከኃላፊነት እንዲነሱና በህግ እንዲጠየቁ አሳስበዋል፡፡