ቻይና የእስያ ሀገራት የዓለማችን ኃያላን መጠቀሚያ ከመሆን እንዲቆጠቡ አስጠነቀቀች
የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ የዓለማችን ኃያላን እንደ "ቼዝ ቁራጭ" ሊጠቀሙባችሁ አይገባም ብለዋል
ዋንግ ዪ “የዚህ ቀጠና እጣፈንታ ሊወሰን የሚገባው በእኛ እና እኛ ብቻ ነው” ሲሉም ተደምጠዋል
ቻይና የእስያ ሀገራት የዓለማችን ኃያላን መጠቀሚያ ከመሆን እንዲቆጠቡ አስጠነቀቀች፡፡
የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ የእስያ በተለይም የደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት የዓለማችን ኃያላን መጠቀሚያ ከመሆን እንዲቆጠቡ አስጠነቀቁ፡፡
የወጭ ጉዳይ ሚኒሰትሩ ይህን ያሉት በዛሬው እለት በደቡብ ምስራቅ እስያ የሚገኙ ሀገራት በተሰበሰቡበት በኢንዶኔዥያ ዋና ከተማ ጃካርታ በሚገኘው የደቡብ ምስራቅ እስያ መንግስታት ማህበር ጽህፈት ቤት ባደረጉት የፖሊሲ ንግግር መሆኑም ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የዓለማችን ኃያላን እንደ "ቼዝ ቁራጭ" ሊጠቀሙባችሁ አይገባም ነው ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ በንግግራቸው፡፡
በርካታ የቀጣናው ሀገራት “በፖለቲካዊ ሁኔታዎች መቀያየር” ስጋት ውስጥ ባለበት ቀጠና ውስጥ እንደመሆናቸው ኃያላን ሀገራት ከጎናቸው እንዲቆሙ በሚል ከፍተኛ ግፊት እያደረጉባቸው መሆኑ ያነሱት ዋንግ፤ ተለዋዋጭ ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት የሚመጣውን ጫና መከላከል ብቸኛ አማራጭ እንደሆነም ተናግረዋል።
“ይህን ቀጠና ከጂኦፖለቲካዊ ስሌት… እንደ ቼዝ ቁራጭ ሊጠቀሙበት ከሚሹ ኃይሎች ልንከላከለው ይገባል” ሲሉም ተደምጠዋል።
የዚህ ቀጠና እጣፈንታ ሊወሰን የሚገባው በእኛ እና እኛ ብቻ ነው ሲሉም አክለዋል የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዪ፡፡
ቻይና የምእራቡ ዓለም ሀገራት በተለይም አሜሪካ በታይዋን ጉዳይ የምታሳየው ጣልቃ ገብነት እና የደቡብ ምስራቅ ሀገራትን መጠቀሚያ ለማድረግ የሚጓዙት ርቀት እንደማትቀበል በተለያዩ ጊዜያት ስትገልጽ የምትደመጥ ሀገር መሆኗ ይታወቃል፡፡