የተመድ ፀጥታው ም/ቤት በኢራን የኒዩክለር ጉዳይ ላይ ተወያይቷል
አሜሪካ ለኢራን ፍላጎቶችና ጥያቄዎች ምክንያታዊ ምላሽ እንድትሰጥ ቻይና ጥያቄ አቀረበች።
ቤጅንግ ይህንን ጥያቄ ያቀረበችው በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ም/ቤት ስብሰባ ላይ ነው። ምክር ቤቱ የኢራንን የኒውክለር ጉዳይ ትናንትና ተወያይቶበታል።
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቻይና ቋሚ መልዕክተኛ፤ ዋሸንግተን ለኢራን የኒዩክለር ቀውስ ተጠያቂ እንደሆነች ገልጸዋል።
አሜሪካ ለኒውክለር ቀውሱ ተጠያቂ መሆኗን ያነሱት የቻይናው የተመድ ተወካይ፤ ዋሸንግተን ቴህራን የምታነሳቸውን ጥያቄዎች በአግባቡና በአወንታዊ መልኩ ማየትና መመለስ እንዳለባት ጠይቀዋል።
በተመድ የቻይና ልዩ መልዕክተኛ ሃንግ ጁን አሜሪካ በኢራን ኒውክለር ጉዳይ ያለባትን ሃላፊነት ፊት ለፊት መጋፈጥ እንዳለባትና ይህንን ስህተት ማረም እንዳለባት ተናግረዋል።
በመሆኑም ሀገሪቷ ፖለቲካዊ ውሳኔ በመወሰንና ተገቢ እርምጃ በመውሰድ ሃላፊነቷን መወጣት እንዳለባት ነው የጠየቁት።
ኢራን በኒውክለር ማብላያ ስራዋ ዙሪያ ከምዕራባውያን ጋር ገብታ የነበረው ስምምነት በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መሰረዙ የሚታወስ ነው።
አሜሪካን ወደ 2015ቱ ስምምነት መመለስ በሚቻልበት ጉዳይ ዙሪያ ሕዳር ወር ላይ ውይይት እንደሚጀመር ከተገለጸ ወዲህ ንግግሩ ሁሉ ስለኢራን ሆኖ ነበር።
የኢራንን የኒውክሌር እንቅስቃሴን የሚገድበውና የተጣሉባትን ማዕቀቦች ለማንሳት የተጀመረው ውይይት እንደሚቀጥል ይጠበቃል።