ቻይና የፌደራል መንግስትና ህወሃትን ማደራደር እንደምትፈልግ ገለጸች
ቻይና ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ጋር ግንኙነቷን የበለጠ ማጠናከር እንደምትፈልግ ገልጻለች
ቻይና ከዚህ በፊት በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ያለመግባት ፖሊሲ ነበራት
ቻይና የፌደራል መንግስት እና ህወሃትን ማደራደር እንደምትፈልግ ገለጸች።
ቻይና በተለይም በምስራቅ አፍሪካ ልዩ መልዕክተኛ በቅርቡ የሾመች ሲሆን ከሌላው የአፍሪካ ክፍላተ አህጉር የተለየ ፍላጎት እና ጥቅም እንዳላት ይገለጻል።
በቅርቡም የምስራቅ አፍሪካ ሰላምና ልማት ጉባኤ በአዲስ አበባ ያካሄደች ሲሆን፤ ቻይና ከምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ጋር ግንኙነቷን የበለጠ ማጠናከር እንደምትፈልግ ገልጻለች።
በምስራቅ አፍሪካ የቻይና ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት አምባሳደር ዢዮ ቢንግ በፌደራል መንግስት እና ህወሃት መካከል ያለውን ልዩነት በማደራደር ወደ ስምምነት እንዲመጡ የማድረግ ፍላጎት እንዳላት ቪኦኤ ዘግቧል።
ቻይና በምስራቅ አፍሪካ ሰላም እንዲመጣ ድጋፍ እንደምታደርግ የተገለጸ ሲሆን በህወሃት እና ፌደራል መንግስት መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ እና ወደ ስምምነት እንዲመጡ ድጋፍ እንደምታደርግ አምባሳደሩ መናገራቸው በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
ይሁንና አምባሳደሩ በሁለቱ አካላት መካከል እንዴት ለማደራደር እንዳሰበች ዝርዝር ነገር ከመናገር ተቆጥበዋልም ተብሏል።
የቻይና አዲሱን አቅድ ተከትሎም ከዚህ በፊት ከነበራት በሀገራት የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ላለመግባት የነበራትን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለውጥ ለማድረጓ ማስረጃ ይሆናልም ተብሏል።
አምባሳደሩ አክለውም “ቻይና በጸጥታ ጉዳይ ስትገባ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው” ያሉ ሲሆን “ቻይና በትብብር የምትሰራው በንግድ እና ኢንቨስትመንት ጉዳዮች ብቻ አይደለም በሰላም ጉዳይም ከሀገራት ጋር በጋራ መስራት ትፈልጋለች“ ሲሉ ተናግረዋል ሲል ቪኦኤ ዘግቧል።
ቻይና በኢትዮጵያ ከ4 ቢሊየን ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው ከ400 በላይ የግንባታ እና ማቀነባበሪያ ፕሮጀክቶች ያሏት ሲሆን በሀገሪቱ ከፈረንጆቹ 2020 ጀምሮ የተከሰተው የብሄር ግጭት የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዋን እያስተጓጎለባት መሆኑ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
ቻይና የፌደራል መንግስትን እና ህወሃትን ለማደራደር ያቀደችው ለብቻዋ ይሁን በአፍሪካ ህብረት ስር ይሁን እስካሁን ያፋ አልሆነም።
ጠቅላይ ሚኒዘስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት እንዳሉት ከህወሃት ጋር ለሚደረገው ድርድር በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የሚመራ ኮሚቴ መዋቀሩን መናገራቸው ይታወሳል።
ሕወሃት በበኩሉ ከፌደራል መንግስት ጋር ለሚደረገው ድርድር ተወካዮቹን እንዳዘጋጀ ገልጾ፤ ድርድሩ በኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እንዲመራ መጠየቁ ይታወሳል።
የትግራይ ክልልን መሰረት አድርገው የተቋቋሙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በበኩላቸው ህወሃት የትግራይን ህዝብ ወክሎ የመደራደር መብት እንደሌለው መናገራቸውም አይዘነጋም።