የትራምፕ ድል ለዩክሬን፣ ለመካከለኛው ምስራቅ እና ለቻይና ምን ማለት ነው?
ተመራጩ ፕሬዝዳንት በውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው በባይደን ዘመን የተከሰቱ ጦርነቶችን አስቆማለሁ ብለዋል
ከቻይና ጋር በሚኖራቸው ግንኙነት ግን አዲስ የንግድ ጦርነት ሊያስነሱ እንደሚችሉ ተሰግቷል
የዶናልድ ትራምፕ ዳግም ወደ ኋይት ሀውስ መመለስ የአሜሪካን የውጭ ፖሊሲን የሚቀይር ነው፤ በተለያዩ የአለም አቀፍ ግንባሮች እና ጦርነቶች ወሳኝ ለውጥ ሊያስከትሉ የሚችሉ ውሳኔዎች ገቢራዊ እንደሚሆንም ይጠበቃል፡፡
በምርጫ በዘመቻው ወቅትም ብዙውን ጊዜ ዝርዝር ማብራርያ ባይኖራቸውም ትራምፕ ሰፋ ያለ የፖሊሲ ማሻሻያዎችን እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡
ለአሜሪካ ቅድሚያ የሚሰጥ ከተለመደው የውጭ ሀገራት ጣልቃገብነት የተገደበ እንዲሁም የንግድ ጥበቃ መርሆዎች ላይ ትኩረት አደርጋለሁ ብለዋል፡፡
በምርጫ ቅስቀሳው ወቅት ከተናገሩት እና ከ2017 እስከ 2021 ባለው ጊዜ ውስጥ በነበራቸው የስራ ልምድ በመነሳት በተለያዩ ወሳኝ አለምአቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ምን አይነት አካሄድን ሊከተሉ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡
ሩስያ ዩክሬን እና ኔቶ
ትራምፕ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ያለውን ጦርነት "በአንድ ቀን" ማቆም እንደሚችሉ ደጋግመው ተናግረዋል እንዴት ተብሎ ሲጠየቁ ድርድሮችን ተግባራዊ በማድረግ ከማለት በቀር ዝርዝር አተገባበሮችን ገልጸው አያውቁም፡፡
በግንቦት ወር በሁለት የትራምፕ የብሄራዊ ደህንነት አማካሪዎች የተፃፈ የጥናት ወረቀት አሜሪካ ለዩክሬን የምትሰጠውን የጦር መሳሪያ ድጋፍ መቀጠል እንዳለበት አመላክቶ ነገር ግን ድጋፉ ኪቭ ከሩሲያ ጋር የሰላም ድርድር እንድትጀምር ቅድመ ሁኔታዎች ማስቀመጥ እንደሚኖርባት ምክረ ሀሳቡን አቅርቧል፡፡
አማካሪዎቹ ሩሲያን ለማባበል ምዕራባውያን ዩክሬን አጥብቃ የምትፈልገውን ኔቶን የመቀላቀል ህልም ማዘግየት አለባቸው ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ዩክሬን ሁሉንም ግዛቶቿን ከሩሲያ ለማስለቀቅ ያላትን ተስፋ መተው የለባትም ነገር ግን አሁን ባለው ግዛቶች ላይ በመመስረት መደራደር ሊጠበቀባት ይችላል ብለዋል።
የዴሞክራት ተቀናቃኞች ትራምፕ ለሩስያው ፕሬዝዳንት ፑቲን ስስ ልብ አለው በሚል ይከሷቸዋል፤ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲውን በተመለከተ የሚያንጸባርቁት ሀሳብም ዩክሬን እጅ እንድትሰጥ የሚገፋፋ እና መላውን አውሮፓን አደጋ ላይ የሚጥል ነው ይላሉ።
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ለዚህ ክስ በሚሰጡት ምላሽ በዩክሬን ጉዳይ ጦርነቱን ማስቆም እና የሚበዘበዘውን የአሜሪካውያን ሀብት ማስቆም ብቻ አላማ እንዳላቸው በተደጋጋሚ ተናግረዋል፡፡
ኔቶን በተመለከተ በመጀመርያው የስልጣን ዘመናቸው የድርጅቱን አመታዊ መዋጮ የማይከፍሉ የአውሮፓ ሀገራት በአሜሪካ ልክ የሚጠበቅባቸውን ገንዘብ የማያዋጡ ከሆነ ድርጅቱን ጥለው እንደሚወጡ አስጠንቅቀው እንደነበር ይታወሳል፡፡
አንዳንድ ደጋፊዎቹ የኔቶ አባላት የሕብረቱን የመከላከያ ወጪ መመሪያዎች እንዲያሟሉ ለማድረግ ጠንካራ የመደራደር ዘዴ እንደሆነ ብቻ በመጠቆም ትራምፕ ከስብስቡ እነደማይወጡ ይናገራሉ፡፡
እውነታው ግን የኔቶ አባል ሀገራት መሪዎች የትራምፕ ድል ለሕብረቱ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምን ማለት እንደሆነ እና ውጤቱም ጠላት ብለው በፈረጇቸው ሀገራት መሪዎች እንዴት እንደሚታይ በከፍተኛ ደረጃ ጭንቀት ላይ ናቸው፡፡
መካከለኛው ምስራቅ
እንደ ዩክሬን ሁሉ ተመራጩ ፕሬዝዳንት የጋዛ እና የሊባኖስ ጦርነትን እንደሚያስቆሙ ቃል ገብተዋል፡፡
በስልጣን ላይ በነበሩበት ዘመን በኢራን ላይ የጣሉት ማዕቀብ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ በማሽመድመድ ለቀጠናው ታጣቂዎች ድጋፍ የምታደርግበትን አቅም አሳጥቷት ነበር በሚል የሚናገሩት ትራምፕ በጦርነቱ ላይ ምን አይነት አካሄድ ሊከተሉ እንደሚችል ግልጽ አይደለም፡፡
ነገር ግን በአዲስ የስልጣን ዘመናቸው በኢራን ላይ ከፍተኛ ጫናን ማድረስ መሰረት ያደረገ ፖሊሲን ሊከተሉ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡
የእስራል ጥብቅ ደጋፊ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ፕሬዝዳንቱ የአሜሪካን ኢምባሲ ከቴልአቪቭ ወደ እየሩሳሌም በማዘዋር ዋና ከተማነቷን አውጀው እንደነበር ይታወሳል፡፡
የአረብ እና የሙስሊም ሀገራትን ከእስራኤል ጋር ለማስታረቅ ጀምረውት የነበረው የአብራሀም አኮርድ ማዕቀፍም ይጠቀስላቸዋል፡፡
ትራምፕ የጋዛን ጦርነት ማስቆም እንደሚፈልጉ በተደጋጋሚ ተናግረዋል ለዚህ ደግሞ ከአረብ ሀገራት መሪዎች ጋር ያላቸውን ወዳጅነት በመጠቀም ሀማስን ወደ ጠረጴዛው ለማምጣት ይችላሉ ተብሏል፡፡
ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚንስትር ኔታንያሁ ጋር ያላቸውም ቅርበት ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል ጠቅላይ ሚንስትሩ በአንድ ወቅት ትራምፕ እስራኤል በነጩ ቤት ካየቻቸው ወዳጆች በሙሉ የሚልቁት ናቸው ሲሉ አሞካሽተዋቸዋል፡፡
ጆባይደን አዘጋጅተውት የነበረውን የጦርነት ማስቆም ሀሳብ ጥቅም ላይ እንደሚያውሉት አልያም በሌላ አዲስ የድርድር ሰነድ እንሚቀይሩት የታወቀ ነገር የለም፡፡
ቻይና እና የንግድ ጦርነት
አሜሪካ ከቻይና ጋር የሚኖራት አቀራረብ ጠቃሚ ከሚባሉ ስትራቴጂካዊ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዎች መካከል አንዱ ነው፡፡
የሀገራቱ ውዝግብ እና ጥል በአለም አቀፍ ደህንነት እና ንግድ ላይ የሚያሳድረው ተጽኖም ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል፡፡
በስልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ትራምፕ ቻይናን “ስትራቴጂካዊ ተፎካካሪ” በማለት ሰይመውታል ፤ ይህን ተከትሎ በአንዳንድ የቻይና ምርቶች የጣሉት የታሪፍ ጭማሪ ቤጂንግም ተመሳሳዩን እንድታደርግ እና የንግድ ጦርነት እንዲጀመር ምክንያት ሆኗል፡፡
ንግድ እና ኢኮኖሚ የትራምፕ ደጋፊዎች ቀዳሚ አጀንዳዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው ከቻይና ጋር በተያያዘ በሚከተሉት የንግድ ፖሊሲ የአሜሪካ አምራቾችን እና ኩባንያዎችን እንደሚጠብቁም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል፡፡
ነገር ግን አሁን ተግባረዊ እየተደረገ ከሚገኝው የታሪፍ ጭማሪ ውጪ አዲስ የንግድ ጦርነት የሚቀሰቀቀስ ከሆነ በቻይና የሚሰሩ እና ምርት የሚያስገቡ የአሜሪካ ኩባንያዎችን እንዲሁም የሁለቱን ሀገራት የምርት ልውውጥ በመጉዳት ኢኮኖሚው ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር እንደሚችል ቢቢሲ ዘግቧል፡፡