ቻይና ከኒዮርክ ቤጂንግ በሁለት ሰዓት ውስጥ መጓዝ የሚችል አውሮፕላን ሰራች
አውሮፕላኑ አሁን ላይ በዓለማችን ፈጣን የተባለውን ኮንኮርድ አውሮፕላን እጥፍ ያህል ይፈጥናል ተብሏል
አሁን ላይ ከኒዮርክ ቤጂንግ ለመብረር እስከ 20 ሰዓት ያስፈልጋል
ቻይና ከኒዮርክ ቤጂንግ በሁለት ሰዓት ውስጥ መጓዝ የሚችል አውሮፕላን ሰራች።
የዓለማችን ሁለተኛዋ ልዕለ ሀያል ሀገር የሆነችው ቻይና ፈጣን የንግድ አውሮፕላን መስራቷን አስታውቃለች።
እንደ ኤምኤስኤን ዘገባ ከሆነ በኒዮርክ እና ቤጂንግ መካከል ያለው ርቀት ከ6 ሺህ 800 ኪሎ ሜትር በላይ ነው።
ይህን ርቀት በሁለት ሰዓት ውስጥ መብረር የሚችል የመንገደኞች አውሮፕላን በቻይናው ሊንግኮንግ ቲያንሺንግ የቴክኖሎጂ ተቋም ተሰርቷል።
ኩባንያው የሙከራ በረራውን ሲያደርግ እንደቆየ ያስታወቀ ሲሆን በቀጣዩ ህዳር ወር ደግሞ የመጨረሻው የሙከራ በረራ እንደሚያደርግ ተገልጿል።
ይህ ሱፐርሶኒክ የመንገደኞች አውሮፕላን ከፈረንጆቹ 2027 ጀምሮ ለገበያ ይቀርባል ተብሏል።
በዓለማችን ላይ ፈጣን የሚባለው በብሪታንያ እና ፈረንሳይ በጋራ የሚመረተው ኮንኮርድ አውሮፕላን ነው።
የመጨረሻ የሙከራ በረራውን እያደረገ ያለው የቻይናው ሱፐርሶኒክ የመንገደኞች አውሮፕላን ከዚህ በፊት የነበረውን የጉዞ ጊዜ በእጥፍ ይቀንሳል።
ከኮንኮርድ ፈጣን አውሮፕላን ውጪ ያሉ መደበኛ የመንገደኞች አውሮፕላን ከኒዮርክ ወደ ቤጂንግ ለመብረር ከ16 እስከ 21 ሰዓታትን ይፈጃል።
ኮንኮርድ አውሮፕላኖች አሁን ላይ ፈጣን ከሚባሉ አውሮፕላኖች መካከል ቀዳሚው ቢሆንም በገበያ ምክንያት ኩባንያው በፈረንጆቹ 2006 ጀምሮ አዲስ አውሮፕላን ማምረት አቁሟል።